ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ አመርቂ ስኬት እየተመዘገበ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ አመርቂ ስኬት እየተመዘገበ መሆኑ ተገለጸ

AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ በከተማዋ የትምህርት ዘርፍ ዙሪያ ለቀረቡ ጥያቄዎች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኃላፊው በምላሻቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የተመዘገቡ አስደናቂ ስኬቶች የመንግሥት፣ የወላጆች እና የጠቅላላው ማኅበረሰብ የተቀናጀ ጥረት ውጤት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኃላፊው እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት የተማሪዎችን ሥነ-ምግባር ከመቅረጽ ባለፈ፣ ያላቸውን ራዕይ ከሀገራዊ እሴቶች ጋር የተሰናሰለ ለማድረግ በትኩረት ተሠርቷል።

የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ወቅቱን የዋጁ እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል። የትምህርት ተቋማትን ውስጣዊ አቅም የማሳደግና የማዘመን ሥራ ለተመዘገበው ስኬት ትልቁን መሠረት ጥሏል።

የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ማለፊያ ምጣኔ ካለፉት ዓመታት ከነበረበት 36 በመቶ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 96 በመቶ ማደጉን ገልጸው፣ ይህም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የተመዘገበ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል።

በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች መካከል ከ30 እስከ 32 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች 50 እና ከዚያ በላይ አምጥተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት መቻላቸውንም ጠቁመዋል።

ይህ ቁጥር በራሱ ቀላል የማይባል መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው የ8 በመቶ አማካይ ማለፊያ ምጣኔ አንፃር ሲታይ፣ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ውጤት የአራት እጥፍ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

ይህ አበረታች ውጤት ሊመዘገብ የቻለው በከፍተኛ ቁጥጥር እና በበይነመረብ ፈተና የታገዘ ሥርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን ዶ/ር ዘላለም አብራርተዋል፡፡

በሂደቱም ኩረጃንና የፈተና ስርቆትን የሚጸየፍ፣ በራሱ አቅምና ጥረት የሚተማመን እንዲሁም ለሀገር የሚሆን ትውልድ መገንባት መቻሉን አብራርተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review