ባለፉት አምስት ዓመታት ስር የሰደዱ የአሰራርና የአደረጃጀት ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing ባለፉት አምስት ዓመታት ስር የሰደዱ የአሰራርና የአደረጃጀት ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

በመዲናዋ ባለፉት አምስት ዓመታት ስር የሰደዱ የአሰራርና የአደረጃጀት ችግሮችን በመቅረፍ፣ ሕዝብን በታማኝነትና በተጠያቂነት የሚያገለግል ዘላቂ ተቋም ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ መደረጉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያና ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ቀደም ሲል መመሪያዎች አንዱ በሌላው ላይ የተደራረቡበትና ለግል ጥቅም ሲባል የማይታወቁ ሕጎች የሚመዘዙበት እንደነበር ከንቲባዋ አስታውሰዋል።

ይህንን አሰራር ለመቅረፍም አስተዳደሩ ባለፉት ዓመታት በተቋም አደረጃጀት፣ በአሰራር ሥርዓት፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ መሠረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አብራርተዋል።

ከፍተኛ የአሰራር ብልሹነት ይስተዋልበት በነበረው የመሬት ዘርፍ ወደ 40 የሚጠጉ የተወሳሰቡ መመሪያዎችና ደንቦች አንድ ወጥ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ለተገልጋዩ ግልጽነትን የፈጠረና በሕግ የተደገፈ አሰራር እንዲሰፍን አድርጓል ብለዋል፡፡

በገቢዎች ዘርፍ አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በተደረገው ርብርብ ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ለውጥ መመዝገቡን ከንቲባዋ አውስተዋል።

በሌላ በኩል፣ የመንግሥት ሠራተኛን በችሎታና በሙያ የመመደብ፣ የአመለካከት ችግሮችን የመቅረፍ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን የመስጠት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ይህ የተቋም ግንባታ ሥራ፤ መሪዎች ቢቀያየሩምና የፖለቲካ ሥርዓቱ ቢለወጥም፣ ሕዝብን በታማኝነትና በተጠያቂነት የሚያገለግል ቋሚ ሥርዓት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ከንቲባዋ አስገንዝበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሕገ-ወጦችና በጥፋተኞች ላይ የተጠያቂነት አሰራርን የማስፈን እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review