አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች መዳረሻ ማድረግ ተችሏል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች መዳረሻ ማድረግ ተችሏል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

አዲስ አበበ የዓለም አቀፍ ስፖርቶች መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ተገኝተው የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አዲስ አበባ አምስት ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት ከተማዋ የዓለም አይን እንዲያርፍባት መደረጉን ገልፀዋል።

በተለይ የነሐስ ደረጃ የተሰጠው “አዲስ አበባ ግራንድ ፕሪ” የአንድ ቀን አትሌቲክስ ውድድር ትልቅ ትኩረት የሳበ ነበር። እንደ ጋቢ ቶማስ የመሰሉ ታላቅ አትሌቶችን ወደ መዲናዋ ያመጣው ውድድር በስኬት መጠናቀቁ የወርልድ አትሌቲክስን ያስደሰተ ነበር።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰናዳችው ይህ ዓለም አቀፍ ውድድር ከነሐስ ወደ ወርቅ ደረጃ እንዲያድግ ወርልድ አትሌቲክስ መወሰኑም ይታወሳል።

በአድዋ ድል መታሰባያ አካባቢ የተደረገው “ሲቲ ማውንቴንባይክ ኤሊሚኔተር ፕሮ ሊግ” የሳይክል ውድድር አዲስ አበባ ሌላ ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲሰጣት ያስቻለ ነበር። ከበርካታ የአውሮፓ ሀገራት የመጡ ተወዳዳሪዎችም በአዲስ አበባ መስተንግዶ እና አጠቃላይ ገፅታ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ ስፖርት በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን ውጤት ያስገኘ ስራ መሰራቱንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጠቅሰዋል።

ከ84ሺህ 678 በላይ ታዳጊ ወጣቶች በከተማ አቀፍ ስልጠና ልማት ፕሮግራም በማሰልጠን 723 ተተኪና ብቁ ስፖርተኞችን ለብሄራዊ ቡድን እንዲሁም ለክለቦች ማፍራት መቻሉም ተገልጿል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ደረጃቸውን የጠበቁ 91 የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎችን ፣ ስፖርት ፓርክን ፣ ለብሔራዊ ጀግኖች ለሆኑ አትሌቶች የአክብሮት ሃውልት ማቆምን ጨምሮ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት በትምህርት ቤት ፣ በመኖሪያ እና መዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም በስራ ቦታዎች በማስፋፋት ሁሉም ዜጎች በአካል እና በአእምሮ ጎልብተው ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ ፣ ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጠናከር መሰራቱንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review