AMN- ሐምሌ 05/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝም፣ በስትራቴጂካዊ የከተማ ትስስር እና ዘመናዊ የከተማ ልማት ዘርፎች አስደናቂ ስኬቶችን ማስመዝገቧን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቀዋል።
ከንቲባዋ ለምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አዲስ አበባ የቱሪስቶች ማረፊያ እና መዳረሻ በመሆኗ በከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ችሏል።
በመዲናዋ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ከነበረበት 4.1 ሚሊዮን ወደ 10.5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥርም ከ123 ሺህ 489 ወደ 1.2 ሚሊዮን በማደጉ ፣ ከውጪ ቱሪስቶች ብቻ ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ ከነበረው 5.63 ቢሊየን ብር ወደ 242.6 ቢሊዮን ብር ማደጉን ከንቲባዋ አስረድተዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማጠናከር በተሰራው ስራም፣ በባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 221 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች በስኬት የተስተናገዱ ሲሆን፣ እንግዶቹ የከተማዋን የልማት ስራዎች እና የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎበኙ ተደርጓል ብለዋል።
የከተማዋ የእህትማማች ከተሞች ትስስር ከነበረበት 20 ወደ 30 ዓለም አቀፍ ከተሞች ማደጉ፣ ለልምድ ልውውጥ እና ለኢኮኖሚ ትስስር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።
አዲስ አበባን ወደ ስማርት ሲቲ የመቀየር ጥረትም ዓለም አቀፍ እውቅናን እያገኘ መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

ከተማዋ በ2024 በደቡብ ኮሪያ የተበረከተውን የሴኡል ስማርት ከተማ ሽልማት፣ በናይሮቢ የተሰጠውን የአፍሪካ ምርጥ ስማርት ከተማ ሽልማት፣ በቦነስ አይረስ ለቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የተሰጠውን የሲ ፎርቲ ከተሞች የብሉምበርግ ሽልማት፣ እንዲሁም በሪዮ ዴ ጄኔሮ የምገባ ፕሮግራም ሽልማት መጎናጸፏን አስታውሰዋል።
አዲስ አበባ የብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ የከተሞች ጥምረት አባል መሆኗን እና በመንገድ ደህንነት ዘርፍም የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኗን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ እነዚህ ስኬቶች የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ በዓለም መድረክ ከፍ እንዳደረጉት ገልጸዋል።
በሚካኤል ህሩይ