በመዲናዋ ከ179 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በመዲናዋ ከ179 ሺህ በላይ ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

ቤት መሰረታዊ ፍላጎትና አንገብጋቢ የህዝብ ጥያቄ መሆኑን በመረዳት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 496 ሺህ 971 ቤቶች መገንባታቸውን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

ከንቲባዋ ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ እንደገለጹት፤ ከተገነቡት ቤቶች መካከል ከ26 ሺህ 563 በላይ የሚሆኑት የመንግስት ቤቶች ለልማት ተነሺዎችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም ከ98 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) በዕጣ ለቆጣቢዎች መታደላቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም የመኖሪያ ቤት እጥረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ በመንግስት፣ በሪል እስቴት አልሚዎች፣ በግል ባለሀብቶች፣ በህብረት ሥራ ማኅበራትና በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት በድምሩ የ179 ሺህ 516 ቤቶች ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል በመንግስት በጀት እንዲገነቡ የታቀዱት የቤቶች ብዛት 50 ሺህ 305 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አማካይ የግንባታ አፈጻጸማቸው ከ30 በመቶ በላይ መድረሱን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለረጅም ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ ላይ ተከማችቶ የነበረውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች የባንክ ብድር ዕዳ ለመክፈል ሰፊ ጥረት መደረጉን ከንቲባ አዳነች ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መሰረት 62 ቢሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ የተከፈለ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የተወሰነ ቀሪ ዕዳ መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በተለያየ ጊዜ ለቤት ግንባታ የተበደረውን የቦንድ ብድር ከመመለስ አንጻርም፣ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 3.18 ቢሊዮን ብር ዕዳ መቀነስ መቻሉን ከንቲባዋ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review