የቤት ኪራይ ጭማሪ ተመኑ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ተደርጎ የተሰራ ነው

You are currently viewing የቤት ኪራይ ጭማሪ ተመኑ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ተደርጎ የተሰራ ነው

AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተወሰነው የቤት ኪራይ ጭማሪ ተመኑ በመዲናዋ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ተደርጎ የተሰራ መሆኑን የከተማዋ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ገለፁ።

የቢሮ ኃላፊዋ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፣ የጭማሪ ጥናቱን ለመተመን ሳይንሳዊ ጥናት መከናወኑን ገልፀዋል።

ጥናቱ አዲስ አበባ ያለውን ችግር መሠረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑንም ነው የጠቀሱት። በዚህም የአሁናዊ የገበያ ሁኔታ፣ የቤት ጥገናና ማሻሻያ፣ የተከራይ የመክፈል አቅም የመሣሠሉት ነጥቦች ከግምት መግባታቸውን አብራርተዋል።

በሁሉም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናሙና በመውሰድ ጥናተቱ መሰራቱንም አስረድተዋል። የቢሮ ኃላፊዋ አያይዘውም፣ የተከራይና አከራይ ደንብና መመሪያው ያለውን ጥቅም ግንዛቤ ፈጥረናል ብለዋል፡፡

በከተማዋ እየተከናወኑ ስላሉ የቤት ግንባታዎች በሰጡት ማብራሪያም፣ አሥተዳደሩ እየገነባቸው ካሉት 50 ሺህ 305 ቤቶች ውስጥ 80 በመቶ ለቆጣቢዎች የሚተላለፉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ በመንግሥት እና በግል በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን 10 ሺህ በላይ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።

መንግሥት ከለውጡ በፊት ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመሠረተ ልማት ሟሟላት ሥራዎችን ማከናወኑንም ገልፀዋል። ቀደም ሲል ከለውጡ በፊት ተገንብተው ሊፍት ያልተሟላላቸውን 5 ሳይቶች በዘጠና ቀናት እቅድ ለመሥራት መታቀዱንና የአንዱ ተጠናቆ የአራቱ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የተረከብነው ያላለቁ የሥራ ዕዳዎች ናቸው ያሉት ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ፣ አሁን በመንግሥት እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎች ግን ይህ ችግር እንደማይገጥማቸው ገልፀዋል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review