AMN- ሐምሌ 5/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም በቀረበው ሪፖርት ላይ በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ በዘርፉ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ አቅርቦት ስብራትን ለመጠገን በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

የገበያ ሥርዓቱን ለነፃ ገበያ ፍላጎት ብቻ ከመተው ይልቅ፣ የከተማ አስተዳደሩ ጣልቃ በመግባት በአሁኑ ወቅት 35 በመቶ የሚሆነውን የገበያ መዳረሻ መሸፈን መቻሉን ኃላፊዋ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የደላላ ጣልቃ-ገብነትን ለመግታት በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ ልዩ የግብይት ማዕከላት መገንባታቸውን የገለጹት ወ/ሮ ሐቢባ፤ በእነዚህ ማዕከላት አማካኝነት ምርቶች ከአምራች በቀጥታ ለሸማች እንዲደርሱ በማድረግ ቀድሞ የነበረውን የአቅርቦት እጥረት መቅረፍ መቻሉን አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት 264 የሚደርሱ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ነዋሪው ሁሉንም የምርት ዓይነቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በአቅራቢያው በአንድ ቦታ እንዲሸምት ማስቻላቸውን ጠቁመዋል።
በ800 የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆችና የንግድ ድርጅቶች አማካኝነት በዘይት፣ በስኳርና በዱቄት ምርቶች ላይ ሰፊ ድጎማ መደረጉን ያነሱት የቢሮ ኃላፊዋ፣ በሕዝብና በግል አጋርነት የተገነቡ 26 ግዙፍ የዳቦ ቤቶች መሬት በነፃ በማግኘትና ከአምራቾች ጋር በመቀናጀት፣ ከነፃ ገበያው ጋር ሲነፃፀር በአንድ ዳቦ ላይ ከ5 እስከ 6 ብር የዋጋ ቅናሽ አድርገዋል ብለዋል።
ወ/ሮ ሐቢባ በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በግብይት ማዕከላቱ እና በ264ቱ የሰንበት ገበያዎች ላይ የነበረውን የደላላ ጣልቃ-ገብነት 100 በመቶ ማስወገድ ተችሏል።

በተጨማሪም በአምስቱ የቁም እንስሳት መገበያያ ሥፍራዎች ላይ ለነጋዴዎች ባጅና ዩኒፎርም በማዘጋጀት የደላላ ጣልቃ-ገብነትን ከ90 እስከ 95 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የንግድ ቢሮ አገልግሎቶች በበይነመረብ የሚሰጡ በመሆናቸው፣ በዜጎች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ሙሉ በሙሉ መቀረፍ መቻሉንም አስረድተዋል።

የንግድ ቁጥጥር ሥርዓቱን ይበልጥ ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር የተጀመረው ዝግጅት መጠናቀቁን የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ የከተማዋ የንግድ ቁጥጥር 100 በመቶ ወደ ዲጂታል ሥርዓት እንደሚሸጋገር ገልፀዋል።
ቢሮው 16 የሚሆኑ አገልግሎቶችን በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማስገባቱንም ጠቁመዋል፡፡
በአስማረ መኮንን