AMN- ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ እየተሰማበት በሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ፣ ከደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ የካራ ብሔረሰብ ተወካይ ወጣት ሙዱ አኮ ለጉባዔው ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
ወጣት ሙዱ አኮ በመልዕክቷ ፤ ለዘመናት በሀገሪቱ ታላላቅና ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የዳር ተመልካች የነበሩት ሴቶች አሁን ላይ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ሀገር እንደጠራቻቸው ገልጻለች።

ይህንን ታሪካዊ መድረክም ለዘመናት እንባ ሲያፈሱ የኖሩ እናቶችና እህቶች ድምፃቸውን የሚያስተጋቡበት ትልቅ ዕድል አድርገው እንደሚመለከቱት አስረድታለች።
ለብዙ ዘመናት እንደ እኛ ያሉ ሴቶች የሀገሪቱን ታሪክ ከሩቅ ቆመን እንመለከት ነበር ያለችው ወጣቷ፤ ሌሎች ይናገሩ ነበር፣ ሌሎች ይወስኑ ነበር ብላለች።

ይህ ድምፅ የእሷ ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሰችው ወጣቷ፤ ለዘመናት ድምፅ ሳይኖራቸው ለኖሩ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን አብዝተው ለሚወዱ እናቶችና ሴቶች ሁሉ ውክልና ያለው መሆኑን በአጽንኦት ገልጻለች።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በውይይትና በንግግር እጥረት ምክንያት የተረፈው ነገር ቢኖር እንባ፣ ጥላቻ፣ ሐዘንና በቀል ብቻ መሆኑን በመግለጽ እሳት ቤት የሚገነባ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በነደደው እሳት ትገነባ ነበር ስትል በምሳሌ አስረድታለች።

ቤት ሊገነባ የሚችለው እጆች በአንድነት ሲተባበሩና ልቦች በቅንነትና በሰላም ሲደማመጡ ብቻ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥታ ተናግራለች።
እንዲሁም ለመመካከርና ለመወያየት ይዛችሁ የመጣችሁትን ጉዳይ እዚሁ ተመካክራችሁ ልትፈቱት ይገባል፤ በዚህ መድረክ ማን ያሸንፋል ብለን አንጠይቅ ይልቁንስ ሁላችንም ተሸንፈን ኢትዮጵያን አሸናፊ እናድርግ ስትል ለጉባዔው ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፋለች፡፡
በበረከት ጌታቸው