ለሸኔ የሽብር ቡድን ተደራሽ ሊሆኑ የነበሩ የመገናኛ ሬዲዮዎች ተያዙ

AMN – ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም

ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ስምሪት በሕገ-ወጥ መንገድ በሞያሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመተላለፍ ለሸኔ የሽብር ቡድን ተደራሽ ሊሆኑ የነበሩ በርካታ የመገናኛ ሬዲዮዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው የመረጃ ስምሪት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴውን ከመነሻው ጀምሮ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥብቅ ሲከታተል የነበረ ሲሆን፤ ለሽብር ቡድኑ እንዲደርሱ ታቅደው የነበሩት የመገናኛ ሬዲዮዎቹ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ለሕግ አካላት ተላልፈው ተገቢው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ገልጿል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተመሳሳይ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ከፀጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ ስምሪት እያደረገ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም በተለያየ መንገድ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በኬንያ አዋሳኝ ቦታዎች በማድረግ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በኩል ወደ ምዕራብ አርሲ ዞን ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ለማድረስ የታቀዱ 98 መገናኛ ሬዲዮዎችና ቻርጀሮቻቸው ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሚያዚያ 12 ፣ 2018 መያዙን አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ አስታውሷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review