AMN- ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ውይይት ከአዳራሽ ተነስቶ እንደ ፀሐይ ወደ መላው ኢትዮጵያ የሚያበራ ከሆነ ለሁላችን ይፈይዳል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ትሆናለች ብለዋል፡፡

ውስጣችን ሰላም እንዲሆን መልካም እንቅልፍ እንድንተኛ ለሰፈሬ፣ ለእኔ ወገን ብላችሁ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብላችሁ እንድትመክሩ በታላቅ ትህትና አደራ እላችኋለሁ ነው ያሉት።
ለዛሬ አትምከሩ፣ ለነገ ምከሩ ለናንተ አትምከሩ፣ ለልጆቻችሁ ምከሩ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን የምንመካከረው ስለትናንትናው አይደለም፤ የትናንትናውን ችግር ፈተን ለነገ መልካም መሠረት ለማኖር ነውና እያንዳንዱ ተወካይ ልጆቹን እያሰበ ለመመካከር የወሰነ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የምክክሩ ስኬት ሙሉ በሙሉ የሚረጋገጠው እርስ በርስ በመደማመጥ እና የሁሉንም ወገን ጥያቄዎች በአክብሮት በማስተናገድ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

ማንም ሳይጎዳ በጋራ መጠቀም የሚቻልባቸውን ጉዳዮች ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ለኔ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ማለት ከቻልን ይህ ምክክር ፍሬያማ ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ቀፎዋን የጣለች ንብ ማር አትሰጥም ማር ለመስጠት በቀፎ ውስጥ መቆየት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬን ሳይሆን ነገ ዘልቆ የሚሄድ ለትውልድ የሚበጅ ምክክር፣ ውይይትና ውጤት ማምጣት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ይህ አራት ሺህ ስብስብ መልካም ነገር መስጠት የሚችለው በዚህ ጉባዔ አዳራሽ ውስጥ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሃሳቡንና ልቡን ሰብስቦ ሌላኛውን ወገን ማድመጥ ሲችል ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ውይይታችን ከዚህ አዳራሽ ተነስቶ እንደ ፀሐይ ወደ መላው ኢትዮጵያ የሚያበራ ከሆነ ለሁላችን ይፈይዳል ብለዋል።
ለጉባዔው ተሳታፊዎችም ይህንን የታሪክ ብራና ሳታባክኑ ለኢትዮጵያ መልካም ለአፍሪካ አስተማሪ የሆነ ሁላችንን የሚሰበስብ ፣ ሰላም የሚያጸና ፣ ልማት የሚያመጣ፣ ለእያንዳንዳችሁ እርካታን የሚያጎናጽፍና ለመላው ኢትዮጵያውያን እረፍት የሚሰጥ ውጤት እንድታመጡ በታላቅ ትህትና አደራ እላችኋለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ላለፉት አራት አመታት በብዙ ችግርና ፈተና ውስጥ ይህ ጉዳይ ለዚህ እንዲበቃ ላደረጉ የምክክር ኮሚሽን አባላትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሻምበል ምህረት