በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ በኩል ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ ተሰርቷል

AMN ሐምሌ 11/2018

በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ በኩል ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የስራ አፈጻጸም ግምገማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ፤ አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች እና እየተለወጠች መምጣቷንና ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆኗን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ፣ የመሬት ወረራን የመከላከል፣ ህገ-ወጥ ግንባታን የመከታተል፣ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቶችን የመቆጣጠር፣ ህገ-ወጥ ንግድን የመከላከል እና ሌሎች ተጨማሪ ተልዕኮዎችን ወስዶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የሚገነቡ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅ በኩል ውጤታማ የደንብ ማስከበር ስራ መሰራቱን ጠቁመው፣ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀትም ከተማዋ ውብ እና ጽዱ እንድትሆን ያስቻሉ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

የመሬት ወረራን በመከላከል እና ህገ-ወጥ ግንባታዎችን በመቆጣጠር በኩልም ስኬታማ ስራ መሰራቱንባ ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከልም እንዲሁ የከተማዋ ጎዳናዎች ከህገ-ወጥ ንግድ ነጻ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።

ባለስልጣኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓቶችን በመጠቀም የቁጥጥር ስርዓቱን ውጤታማ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፣ የደንብ ጥሰቶች ይፈጸሙባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች ካሜራዎችን በመግጠም ከሲቹዌሽን ሩም በመሆን የዕለት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል የከተማዋን ስታንዳርድ ከማስጠበቅ አንጻር በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በከተማዋ ወጥ የሆነ የቀለም ስታንዳርድ መውጣቱን ተናግረው፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ዙሪያም በየአመቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አልሚዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት አምስት አመታት አዲስ አበባ በመዋቅራዊ ፕላኗ ብቻ እንድትመራ መደረጉን ጠቁመው፣ ህገ-ወጥ ግንባታዎች እንዲቀሩ በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡

የማስታወቂያ ቦርዶችን ዲጂታል ለማድረግ የተከናወኑ ስራዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት መፍጠራቸውን በመግለጽ።

በቀጣዮቹ ጊዜያትም የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ልማቱን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰራ ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review