የ”ጎቤ” እና “ሺኖዬ” ጨዋታ

You are currently viewing የ”ጎቤ” እና “ሺኖዬ” ጨዋታ

AMN – ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም

ከክረምት ወደ ጸደይ ወቅት መሸጋገርን የሚያበስረው “የጎቤ” እና “ሺኖዬ” ባህላዊ ጨዋታ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

ወጣቱ ትውልድ የዘንድሮውን የጎቤ እና ሺኖዬ በዓልም ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ነው እያከበረ የሚገኘው፡፡

በኦሮሞ ባህል ዘንድ የክረምቱን መውጣትና የጸደይ መዳረሻን ለማብሰር ከሚከናወኑ ባህላዊ ሥርዓቶች መካከል “የጎቤ” እና “ሺኖዬ” ጨዋታ ተጠቃሽ ነው።

የ”ጎቤ” ባህላዊ ጨዋታ በዋናነት ወጣት ወንዶች ከክረምት ወደ ጸደይ መሸጋገርን በማስመልከት የሚጫወቱት ነው።

ጎቤ፤ በወጣት ወንዶች ዘንድ ጀግንነትን፣ ፍቅርን፣ ድልን እና የላቀ ተስፋን የሚያንጸባርቅ ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን ወጣቶቹ በቡድን ሆነው በድምቀትና በሰልፍ እርምጃ እየጨፈሩ የዘመኑን መለወጥ ያበስራሉ፡፡

”ሽኖዬ” ደግሞ በወጣት ሴቶች የሚከወን ሲሆን የዋህነትን፣ ውበትን፣ ሰላምን እና አዲስ ተስፋን ያበስራል፡፡ ልጃገረዶቹ በባህላዊ አልባሳት አጊጠው የሚከውኑት በደስታ እና በፈገግታ የታጀበ የውበት እና የህብረት ጨዋታ ነው።

የጎቤ እና ሺኖዬ የሚጨፍሩ ወጣቶች በእጃቸው እርጥብ ሳርና አበቦችን በመያዝ በየቤቱ እየተዘዋወሩ የልምላሜ፣ የሰላምና የብልጽግና መልካም ምኞት ያስተላልፋሉ።

ወጣቶቹ ማህበራዊ መስተጋብርን፣ ሰላምን እና የትውልድ ቅብብሎሽን በሚያሳይ መልኩ ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ መልካም ምኞታቸውን ለህብረተሰቡ ይገልጹበታል፡፡

ማሕበረሰቡም ወጣቶቹን በማበረታታት አብሮነቱን ያረጋግጣል፤ ይህ መስተጋብርም በህብረተሰቡ መካከል ያለውን ፍቅር፣ መከባበርንና አብሮነትን ከፍ ያደርጋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት የሚከበረው ይህ ታላቅ ባህላዊ ሁነት ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክርና የህብረተሰቡን ጥልቅ እሴቶች እያደመቀ የሚገኝ የተፈጥሮን ውበት የሚያንጸባርቅ ነው።

የጎቤ እና ሺኖዬ ባህላዊ ስርዓት የይቅርታ፣ የፍቅርና የዕርቅ እሴትን በማጎልበት ረገድ ማሕበራዊ ፋይዳው የላቀ ነው።

የጎቤ እና ሽኖዬ ባህላዊ ጨዋታዎች መስፋፋትም የኦሮሞን ህዝብ እሴት ለትውልድ ለማሸጋገር ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህን መሰሉ ባህላዊ እሴት መጎልበት የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብት ከማስፋቱም በላይ የህዝቦችን ትስስርና አንድነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደዚህ ያሉ ታላላቅ ባህላዊ ስርዓቶች እንደ ኢሬቻ ካሉ በዓላት ጋር ተሳስረው በድምቀት እየተከበሩ ይገኛል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review