AMN -ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ14 በላይ ሀገራት የሚሳተፉበትን መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ የአፍሪካ ዋንጫን ከህዳር 21 እስከ ታህሳስ 4 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የምታስተናግድ ይሆናል።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ማህበር አመራሮች ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ማግኘታቸው ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነትና ኩራት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ደጀኔ ሀብታሙ ውድድሩን በስኬት ለማጠናቀቅ የሁሉም አካላት ትኩረትና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ለዝግጅቱ ስኬት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በማህበሩ መካከል የመግባቢያ ሰነድ መፈራርማቸውን ገልጸዋል።
የስምምነቱ ዋና አላማም መስማት የተሳናቸውን እግር ኳስ በስፖርታዊና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማሳደግ የሀገር ውስጥና የአህጉር አቀፍ ውድድሮችን በስኬት መወጣት በቴክኒክ፣ በውድድር፣ በአቅም ግንባታ፣ በስልጠና እና በመሰረተ ልማት በቅንጅት መስራት እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ማህበር ዋና ጸኃፊ አቶ በላቸው ስሜነህ በበኩላቸው፣ ይህ ታሪካዊ ውድድር መስማት የተሳናቸውን ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የሚጠይቅ ነው ብለዋል::
በኦብሲኔት ክፍሌ