AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

የዘመን መለወጫ በዓልን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን አላስፈላጊ የዋጋ መዋዠቅ ለመከላከል እና የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ለማቃለል የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሐቢባ ሲራጅ በሰጡት መግለጫ፣ ለበዓሉ በንግድ ሥርዓቱ ላይ እክል እንዳይፈጠር ከሁለት ወራት አስቀድሞ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመው ፣ ምርቶች በቂ አቅርቦትና ሰፊ ተደራሽነት እንዲኖራቸው አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን አብራርተዋል።
ኃላፊዋ እንደገለጹት ፣ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የገበያ ማዕከላት፣ የቁም እንስሳት መገበያያ ቦታዎች እንዲሁም ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው የኤግዚቢሽንና ባዛር መድረኮች ይዘጋጃሉ።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን በሱቆቹ በኩል ለበዓል የሚሆኑ መሠረታዊ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ምርቶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን የገለጹት ኃላፊዋ ፣ ሕገወጥ ንግድን ለመከላከልና በዓሉን ያለምንም ችግር ለማሳለፍ ጥምር ግብረ ኃይል የመጋዘን ፍተሻ እና ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
በዘይት፣ በነዳጅ እና በእንስሳት ገበያ ላይ የሚታየውን የደላላ ሰንሰለት በመስበር የገበያውን ሁኔታ ማረጋጋት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሐቢባ፣ የምርት ጊዜ ያለፈባቸው ዕቃዎች ለገበያ እንዳይቀርቡ ጥብቅ ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የልኬት እና ሚዛን ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድም የቁጥጥር ግብረ ኃይሉ የተጠናከረ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የንግድ ቢሮ ባለሙያዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በዓሉ እስኪያልፍ ድረስ በመደበኛ እና በመንግስት በሚመቻቹ የገበያ ስፍራዎች ላይ ልዩ የክትትል ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
በአብዱሰላም አንሳር
See less