AMN-ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የነበረው የ2018 በጀት ዓመት እና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዳ አፈፃፀም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
በግምገማውም የታቀዱ ስትራቴጂክ ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር 24/7 በተለወጠ የስራ ባህል በትጋት መስራት በመቻሉ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማላቅ እና የተለዩ ድክመቶችን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአገልግሎት አሰጣጣችን ዲጅታላይዝ በማድረግ በተለይም ደግሞ በያዝነው በጀት ዓመት ተግባራዊ ያደረግነው በመሶብ ዲጅታል የአንድ ማዕከል የመንግስት እገልግሎት ትራንስፎርም አድርገናል፥ ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ ማንንም ያልዘነጋ ህፃናት ፥ ተማሪዎች ፥ ሴቶች፥ ወጣቶች ፥ አረጋውያን ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ልማቶችን አስተዳደራቸው በትጋት መስራቱን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች 2.2 ሚሊዮን የስራ ዕድል የፈጠርንበት፥ የልማቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን የገቢ አሰባሰብ ስርዓትም እጅግ ውጤታማ የነበረበት፥ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት የተፈፀመበት፤ መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ፣ ሀገራዊና አህጉራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ ሚናዋን በብቃት የምትወጣ ፤ አዲስ አበባ ስሟና ግብሯ የተናበበ ፅዱ ፥ አረንጓዴና ውብ ከተማ የማድረግ፤ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትታይ በማላቅ የተፈፀመበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል።

ከንቲባ አዳነች ባሰፈሩት መልዕክት አክለውም “ከስኬቶቻችን ባሻገር ዛሬም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች የአመራራችን የውጤታማነት ልዩነቶች፣ የስነምግባር መጓደል፣ የመረጃ አያያዝ ክፍተቶችን ለማረም እንሰራለን፤ እንዲሁም በቀጣይ የኑሮ ውድነት እና የገበያ ማዛባትን ማስተካከል፥ የስራ እድልን ማስፋት፥ ፅዳትን ባህል ማድረግ፥ አገልግሎትን ማዘመን ፣ የመሶብ ዲጅታል አንድ ማዕከልን ማጠናከር፣ የቤት፥ ትራንስፖርት፥ መንገድ፥ ውሃ አቅርቦት ማሻሻል፥ የከተማ ማደስ በአጠቃላይ የጀመርነውን ልማት በጥራት፣ በስፋትና በፍጥነት አጠናክረን እንሰራለንም ብለዋል። ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው ጠንካራ መንግስት የመመስረት ስራም ልዩ ትኩረት የሚሰጠዉ እና የመረጠንን ህዝብ ይበልጥ በቅንነት ፣ በታማኝነትና በትጋት የምናገለግል መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን ሲሉ ገልፀዋል።