AMN – ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
የተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት የተቋም ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ስርዓትና የልማት ከፍታ የተረጋገጠበት ዓመት ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋና ጽ/ቤት የዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚንስትር ዴኤታዎች፣ የቅ/ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ አደም ፋራህ እንደገለፁት፤ የ2018 በጀት ዓመት በተቋም ግንባታ፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት እና በልማት ሥራዎች ጉልህ ውጤቶች የተመዘገቡበት ዓመት ነው።
በጀት ዓመቱ ከፓርቲ ግንባታ አኳያ ብልፅግና በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በሰብዓዊና ቁሳዊ ሀብት እንዲሁም በማስፈጸም አቅሙ ተጠናክሮ የወጣበት ዓመት መሆኑን የተናገሩት አቶ አደም ፋራህ ድርብርብ ተልዕኮዎችን በታቀደው መሰረት ማሳካት የተቻለበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
መላው ሕዝባችን በእያንዳንዱ ተልዕኮ ላይ በንቃት በማሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በመደረጉና በባለቤትነት ስሜት ከፓርቲያችን ጎን በመቆሙ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዟችን ጠንካራ መሠረት የጣለውን 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ መንታ ግቦች በላቀ አፈጻጸም ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

ልማትና ዴሞክራሲን ጎን ለጎን በማስኬድ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት የላቀ ውጤት መመዝቡን የገለፁት አቶ አደም ፋራህ፤ የፓርቲውን ግዙፍ አቅም አሟጦ በመጠቀምና የአመራር ስነ ምግባር ልህቀትን በማረጋገጥ የሕዝባችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አክለውም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ያብራሩ ሲሆን የአመራርና አባላት ጥራት ማረጋገጥ፣ የብሄራዊነት ገዥ ትርክት ማስረጽና የፓርቲ ተቋማዊ ስታንዳርዳይዜሽን ስርዓት ግንባታ ላይ በተጠናከረ መንገድ ይሰራል፣ ለዚህም የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና የመላው ሕዝብ ርብርብ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ በ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርት እና በ2019 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ላይ ጥልቅ ውይይት እንደሚደረግ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችም እንደሚቀመጡ ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡