AMN – ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም
አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያገግሙና የተሰደዱ የዱር እንስሳት እንዲመለሱ ማስቻሉን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በአድዋ ድል መታሰቢያ እያከበረ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ፤ እንደ ሀገር ከዱር እንስሳት ጥበቃ ጋር የተያያዙ ስራዎች ቀድመው የተጀመሩና ረጅም አመታትን ያስቆጠሩ ቢሆንም፤ ለዘርፉ የነበረው ወጥ ያልሆነ ትኩረት ሀገሪቱ መድረስ ከነበረባት ስፍራ እንዳትደርስ አድርጎ ቆይቷል ብለዋል።

ሆኖም ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር፤ በመጥፋት ላይ የነበሩ የተፈጥሮ ሀብቶች እንዲያገግሙና የተሰደዱ የዱር እንስሳት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማስቻሉን ገልፀዋል።
ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር ፣ ገበታ ለትውልድ እና ሌሎች መሰል ኢኒሼቲቮች የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅና የቱሪዝም ዘርፉን ለማስፋፋት አጋዥ ኃይል መሆናቸውን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
እንዲሁም በከተሞች እየተገነቡ የሚገኙ ፓርኮች፤ በከተማ የሚኖረው ማህበረሰብ ስለዱር እንስሳት የነበረውን ቁጥብ ግንዛቤ እንዲያሰፋ እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት 60 ዓመታት የዱር ሀብቶችን ለመጠበቅ የተደረገው ጉዞ በበርካታ ተግዳሮቶች የታለፈ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ ናቸው።
ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት ለተፈጥሮ ሀብት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በላይሁን ፍስሃ