AMN ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም
ህወሃት የትግራይን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ በሚል ከትጥቅ ትግል ተነስቶ ሃገር እስከ መምራት የደረሰ የፖለቲካ ፓርቲ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ግን በአላማም በፖርቲም ተከፋፍሎ በአጠቃላይ የፖለቲካ ህይወቱ በፈጣን የኋሊት ጉዞ ላይ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን ነጻ አወጣሃለሁ የሚለዉን ህዝብ መልሶ የሚጨቁን: የትግራይ እናቶችን የሚያስለቅስ የጽንፈኞችና የህገወጦች መሰብሰቢያ መሆኑን በተግባር በማስመስከር ላይ ይገኛል።
ወጣቶችን ለጦርነት ከመጠቀም ዉጪ የትግራይን ክልል ከጦርነት፤ ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ነጻ አዉጥቶ የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ያልቻለዉ ይህ ቡድን ዛሬም ለትግራይ ህዝብ ልማትና ነጻነት የቆምኩት ብቸኛዉ ታጋይ እኔ ብቻ ነኝ በማለት የሃሰት ትርክቱን በመንዛት ላይ ይገኛል።
በልማት ያላሻገረዉን ህዝብ ለጦርነት ብቻ የሚፈልገዉ ጽንፈኛዉ ህወሃት: እንደ ሻዕቢያና ግብጽ ያሉ የጥፋት ኃይሎችን ወዳጅ በማድረግ ክልሉን የጦርነትና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ እየተጋ ይገኛል።
ትናንት የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ያገባናል፣ ይመለከተናል ብለዉ ሲምሉና ሲገዘቱ የነበሩ የጽንፈኛዉ ቡድን አመራሮችም ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ የልማትና የሠላም ሃይሎችን በከሃዲነት ይከሳሉ።
እዉነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለዉ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ መላዉ ኢትዮጵያዊያን የዚህ ጽንፈኛ ቡድን ዋንኛ አላማ ተረድተዉ በማዉገዝ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አበባን ጨምሮ በአዉሮፓ፤ አሜሪካ እና በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚኖሩ ትግራዋይ የዚህን ህገወጥ ቡድን ጸረ ኢትዮጵያዊ አቋም ተረድተዉ ማዉገዝ መጀመራቸዉም የቡድኑ አላማ ሃገር ማፍረስ መሆኑን በመረዳታቸዉ ነዉ።
ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ከሻዕቢያ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እናት ሀገሩን የሚወጋ የጽንፈኞች መሰብሰቢያ እንጂ የትግራይን ህዝብ ከድህነትና ኋላ ቀርነት የሚያወጣ የህዝብ ልጅ አለመሆኑን በበርካቶች ዘንድ እምነት ተይዟል።
ይህ ቡድን የትግራይን ወጣቶች ለትምህርት፤ ለስልጠናና ለቴክኖሎጂ የሚያዘጋጅ ሳይሆን ህጻናትን ለጦርነት አፍኖና አስገድዶ የሚወስድ የማፊያዎች ቡድን መሆኑ በተጨባጭ ተረጋግጧል።
ይህ ቡድን የትግራይ ከተሞች በግጭትና ጦርነት በልማት ወደ ኋላ እንዲቀሩ ከማድረግ ዉጪ እንደ አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት የማስዋብ ዕቅድም ሆነ ህልም እንደሌለዉ በተግባር ታይቷል።
ይህ ቡድን የክልሉን ወጣቶች በግዳጅ አፍሶ ወደ ጦር ግንባር ከመዉሰድ ዉጪ በመዲናዋ የልማት ስራዎች ተሳትፈዉ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸዉ የሚፈልግም አይደለም።
ቡድኑ እንደ ሻዕቢያና ግብጽ ላሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚላላክ: ወርቅን ጨምሮ የክልሉን ሃብት የሚዘርፍ፣ የሚቃወሙትን የሚያስፈራራ፣ የሚያስርና የሚገድል የነዉጠኞች ስብስብ ሆኗል።
ቡድኑ በሃሳብ የበላይነት የማያምን፣ ከጦርነትና ከግጭት ጋር ተወልዶ በዚሁ ህመም ምክንያት ወደ ኋሊት እያሽቆለቆለ የሚገኝ ጸረ ልማትና ሠላም ሆኗል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎችን ጨምሮ የአፍሪካና የአለም አቀፉ ህብረተሰብ አባላትም ይህ ቡድን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናዉ ሠላምና ደህንነት አስጊ መሆኑን አምነዉ ማዉገዛቸዉም የህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የኋሊት ጉዞ ከማንም በላይ ነጻ አወጣሃለሁ የሚለዉን የትግራይን ህዝብ የሚጎዳ በመሆኑ ነዉ።
ከወጣትነቱ እስከ እርጅናዉ ከስህተቱ መማር ያልቻለዉ ጽንፈኛዉ ህወሃት በዚህ አካሄዱ ክልሉን ወደ የት ሊወስደዉ ይችላል?
ከንግግርና ከምክክር ዉጪስ በጦርነትና በግጭት የሚፈታ ችግር ይኖር ይሆን?
በወንድማገኝ አሰፋ