AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
እኛ የወደፊቱን ዕጣ ፈንታችንን እና መዳረሻችንን ሌሎች እንዲወስኑ አንጠብቅም አንፈቅድም፤ ይልቁንም በሀገራችን ጥበብ፣ በራሳችን ዕውቀት እንቀርጸዋለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ዛሬ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያዎቹን የAI ስታርትአፕ ሠልጣኞች በሳይንስ ሙዚየም በድምቀት አስመርቀናል ብለዋል።

ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዘርፉ የሰጡት ልዩ ትኩረትና የቅርብ ክትትል ፍሬ፣ እንዲሁም ሀገራችን በልጆቿ ጥረት ያስመዘገበችው ትልቅ የስኬት ምዕራፍ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በስማርት ሲቲ፣ በፋይናንስ እና በሌሎችም ዘርፎች የተሠማሩት እነዚህ ወጣት ፈጣሪዎች፣ የቴክኒክና የምርት ልማት ክሂሎት፣ ትክክለኛ ችግር ፈቺ የቢዝነስ አስተሳሰብ፣ ደረጃውን የጠበቀ የAI ወርክሾፕ፣ የክላውድ ዳታ ማዕከል እና ከፍተኛ የኮምፒዩቲሽናል ሪሶርስ ድጋፍ አግኝተዋል ብለዋል።

አንድ ስታርትአፕ ሲደገፍ የላቀ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ መንግሥታችን ለዚህ ትኩረት ሰጥቷል፤ የዛሬ ተመራቂዎችም ተጨባጭ ማሳያ ናቸው ሲሉም አንስተዋል፡፡