AMN- ሐምሌ 20 /2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ውስጣዊ እና ዉጫዊ ፈተናዎችን በጽናት እና በቁርጠኝነት አልፋለች፡፡
ለብሔራችንና ለሀገራችን የተሻለ መንግስታዊ ሥርዓት እንፈጥራለን በሚል የፖለቲካ ዓላማ መንቀሳቀስ ጀምረው ሀሳባቸው ህዝባዊ ተቀባይነት ሲያጣ፣ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን ተሰልፈው የተገኙ፤ ብሎም የገዛ ሀገራቸውን የወጉ ኃይሎች እንደነበሩም የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውን ሲወጉ ከነበሩና ዛሬም እየወጉ ከሚገኙ ኃይሎች መካከል ደግሞ ሻዕቢያ ቀዳሚው ነው፡፡
ሻዕቢያ በህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ትከሻ ላይ በመቆምና ግብጽን ለመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በመላላክ ኤርትራ እንድትገነጠል ያደረገ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የባህር በር እንድታጣ ትልቅ መንስኤ ሆኗል፡፡
የትግራይን ህዝብ ነፃ አወጣለሁ በሚል የፖለቲካ ዓላማ ለግማሽ ዘመን በትግል ላይ የሚገኘውና በኢትዮጵያዊነቱ የማያምነው ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን፣ ያለ ኢትዮጵያዊያን ይሁንታና ፈቃድ ኤርትራ እንድትገነጠል፤ ኢትዮጵያም የባህር በር እንድታጣ ተባባሪ በመሆን ታሪካዊ በደል ፈጽሟል፡፡
ከታሪካዊ ስህተቱ የማይማረው ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን፣ ከዓመታት በፊት በሰሜን ዕዝ ተጨማሪ ታሪካዊ በደል የፈጸመ ሲሆን፣ በከፈተው ጦርነት ምክንያትም ከፍተኛ የህይወትና የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ የትግራይ ክልል ሰላምና ልማትም እንዲደናቀፍ ትልቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
ጦርነቱ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተቋጭቶ፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የትግራይን ክልል ሰላምና ልማት ወደ ቀድሞው ለመመለስ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በኃይል በመፈንቀል ሌላ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሟል፡፡
ይህ ቡድን በአሁኑ ወቅት ሻዕቢያ እና ግብጽን ከመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ህልውና በመገዳደር ላይ ይገኛል፡፡
ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን በተደጋጋሚ የሚፈጽማቸው ጥፋቶችና በደሎች የቤቱን ምሰሶ የማፍረስ ዓላማ እንጂ፣ የቤቱን ቀለም የመቀየር ዓላማ እንደሌለው የክልሉ ተወላጆች፣ ምሁራን፣ ፓለቲከኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታጣቂዎች የሚያደርጉትን ትግል አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በየትኛውም አካባቢ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል ብልጽግና ፓርቲ ይውደቅ ማለት ይችላል፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣ ፖርቲዎች እና ግለሰቦች እንዲቀያየሩ መጠየቅና የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ ማስገባት የተለያየ ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህም በራስ እግር ላይ እንደመተኮስ ይቆጠራል በማለት ነበር የገለጹት፡፡
የጠላቶቻችን ፍላጎት ምሰሶውን ማፍረስ እንጂ ቀለም መቀየር አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የባንዳዎቹ ችግር የቤቱን ቀለም ለመቀየር የሚደረግ ትግልን ምሰሶ ለማፍረስ ከሚደረግ ትግል ጋር መቀላቀላቸው እንደሆነ ማንሳታቸውም ይታወሳል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ