የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የምክክር ባህልን ማዳበር ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ

AMN- ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ለዘመናት ስር የሰደዱ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያካሄደች ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በስኬት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በሰጡት አስተያየት፤ ሀገርን ለማጽናትና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ የውይይትና የምክክር ባህልን ማዳበር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የአይነ ስውራን አካቶ ትምህርት አስተባባሪ አቶ ከተማ ባይለይኝ እንደተናገሩት፤ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር የሚደረግ መመካከር፣ መነጋገርና የሀሳብ ልውውጥ በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡

የሀሳብ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ውይይት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ በዚህም የተለያዩ ቡድኖች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በመቀመጥ የጋራ ጥቅማቸውን ማስከበርና በጋራ ማደግ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ምክክር ዜጎች “የእኔ ጉዳይ ያንተ ጉዳይ ነው፤ ያንተ ጉዳይ ደግሞ የእኔ ጉዳይ ነው” የሚል የጋራ ስሜት እንዲያዳብሩ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

መመካከር ማለት ልዩነቶችን ወደ ኋላ በመተው አንድ በሚያደርጉ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መፍጠር ነው ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት ባይሳ ናቸው።

በተመሳሳይ የግለሰብ ራዕይ ከሀገር ሰላም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን ያነሱት አቶ ባስሌል ስለሺ ሀገር ሰላም ከሆነች መስራትና መለወጥ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

አክለውም በየትኛውም ሁኔታ መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በምክክር ሂደት ውስጥ ችግሮችን በመለየት ተገቢውን መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ፓስተር ሰርጉ አለሙ በበኩላቸው ፤ ስንደማመጥ ፣ ስንመካካር እና በውይይት ችግሮቻንን መፍታት ስንችል ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ አጠናክራ ትቀጥላለች በማለት መመካከር ለሀገር ግንባታ ያለውን አስተዋጽኦ አብራርተዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች አሁን እየተካሄደ ያለው ሃገራዊ የምክክር ጉባዔ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም ዜጋ ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

በትዝታ መንግስቱ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review