AMN – መስከረም 5 / 2019 ዓ.ም
የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራትና የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘህራ መሐመድ ከኳታር ንግድ ምክር ቤት ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር ራሺድ ቢን ሐማድ አል-አዝባ እና ከሌሎች የምክር ቤቱ የቦርድ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዘህራ መሐመድ በኢትዮጵያ አሁን ላይ የተፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት ምኅዳር፣ መንግሥት የተገበራቸውን አበረታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲሁም ለውጭ ባለሀብቶች የተዘጋጁ ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን አስረድተዋል።
በተለይም በግብርና፣ በጤና እና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ያሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ባለሀብቶቹ ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
ከዚህም በተጨማሪ በቅመማ ቅመም፣ በሥጋ፣ በአበባ፣ በቡና፣ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ንግድ ዘርፎች የሚገኙ ትሩፋቶችን እንዲጠቀሙና የንግድ ግንኙነቱ ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
የኳታር ንግድ ምክር ቤት ሁለተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ሚስተር ራሺድ ቢን ሐማድ አል-አዝባ በበኩላቸው፣ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሚገኙትን ሰፊና አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ለመጠቀም ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት የንግድ ልዑካን ቡድን የዕርስ በዕርስ ጉብኝቶችን ማጠናከር እና የጋራ የንግድ ፎረሞችን ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በሁለቱ ሀገራት የንግድ ምክር ቤቶች መካከል የጋራ ካውንስል ቢቋቋም የሁለትዮሽ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና ሁለቱንም ወገኖች ተጠቃሚ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኳታር ምክር ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጠቁመዋል።
የሁለቱን ሀገራት ምክር ቤቶች መልካም ግንኙነት ከፍ ለማድረግ እና ለነበረው ፍሬያማ ቆይታ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የኳታር ንግድ ምክር ቤት ለወ/ሮ ዘህራ መሐመድ የክብር ማስታወሻ ስጦታ ማበርከቱን በዶሃ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተገኘው መረጀ ያመላክታል።