AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ ታሪካዊ የሥራና የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራርሟል።

ድርጅቱ ከፈረማቸው ስምምነቶች መካከል ከአባ ለታ አክቲንግ አካዳሚ ጋር ያደረገው ስምምነት አንዱ ሲሆን ስምምነቱ በኪነ-ጥበብ ስራዎች፣ በክህሎት ግንባታ፣ በኩነቶች ዝግጅት፣ በባህልና በሌሎችም መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ድርጅቱ ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ዝክረ ታሪክ ጽሕፈት ቤት ጋር የትብብር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል፡፡

እንዲሁም የደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶን ገድልና አኩሪ ታሪክ የሚያወሳውን ታሪካዊ ቴአትር በጀግናው የትውልድ ስፍራ ወሊሶ ከተማ ለእይታ ለማቅረብ ከወሊሶ ከተማ አስተዳደር ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡

ይህ ስምምነት እውን ሊሆን የቻለው ከደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ቤተሰቦች ጋር በተደረገ የጋራ ትብብር መሆኑን የድርጅቱ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የ”ባልቻ አባ ነፍሶ” ቴአትር በቅርቡ ለወሊሶ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በመድረክ እንደሚቀርብ የተጠቆመ ሲሆን በከተማዋ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰራም ተመላክቷል፡፡
እነዚህ አዳዲስ አጋርነቶች የጀግኖችን ታሪክ በኪነ-ጥበብ ህያው አድርጎ ለትውልድ ለማስተላለፍና የሀገሪቱን የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ያጠናክራሉ ተብሎ ይታመናል፡፡