የሕዝቦች ለዘመናት የዘለቀ ውህደት እና የጋራ አስተዋጽኦ ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ መሠረት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት አብሮ የመኖር፣ የመጋመድ እና በጋራ የማደግ ታሪክ ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሚኮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፣ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ የብሔረሰቦች መስተጋብር የነበረውን ቦታ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች በሙሉ በዘመናት መካከል አብረው በመኖር ፣ በጋብቻ፣ በንግድ እና በህይወት አጋጣሚዎች በስፋት የተሳሰሩና የተጋመዱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በተለይም የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን አቀማመጥና የህዝብ ቁጥር መሠረት በማድረግ፣ መስተጋብራቸው በሦስት ዋና ዋና መንገዶች በስፋት የተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በንግድ፣ በውጊያ እና በስራ አጋጣሚዎች በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሕዝብ ለሕዝብ እና የግለሰቦች አንዱ ከአንደኛው ጋር የመዛመድ እና የመጋባት ሰፊ ልምምድ እንደነበረ ነው የጠቀሱት።

በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ እና የሲቪል ስልጣንን ለማጽናት ሲባል ሰፋፊ የፖለቲካ ጋብቻዎች ይፈጸሙ እንደነበርም አንስተዋል።

በታሪክ ውስጥ በነገሥታት ደረጃ ጭምር በጉዲፈቻ አማካኝነት ባህልን የመጋራት፣ አብሮ የማደግ እና የጠበቀ ማህበራዊ ትስስር የመፍጠር ልምድ የቆየ መሆኑን አስረድተዋል።

በታሪክ ሂደት የነበረውን የሕዝቦች ስብጥርና መጋመድ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ ለ350 ዓመታት ያህል በቆየው የሸዋ ሱልጣኔት ዘመን ኦሮሞች፣ አማሮች፣ አርጎባዎች፣ ጉራጌዎችና ሌሎችም ብሔሮች በጋራ ይኖሩበት እንደነበርና በዚያ ረጅም ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መጋመድ እንደነበረ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ ከ130 ዓመታት በላይ የቆየውና ከሸዋ እስከ ዘይላ ይዘረጋ የነበረው የኢፋት ሱልጣኔትም ከፍተኛ የሆነ የሕዝቦች መስተጋብርና ውህደት የታየበት እንደነበር ተናግረዋል።

በአፄ ሱስንዮስ፣ በአፄ ባካፋ እና በአፄ እያሱ ዘመን የነበሩትን የታሪክ አጋጣሚዎች፣ እንዲሁም የየጁ እና የወረሂመኖ ስርወ መንግሥታትን እንደ ማሳያ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕዝቦቹ አብረው በጋራ የሰሩበትን፣ የተዋጉበትን እና ሀገር ያደመቁበትን የታሪክ ማህደር የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ውስጥ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የራስ ጎበና ዳጬ ውህደት ወሳኝ ሚና እንደነበረው የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ጥረት እና የተገኘው የጋራ ውጤት ዘመናዊቷን ሀገር ለመፍጠር መሠረት መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዓድዋ ድል ያሉ የሀገሪቱ ኩራቶችም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ የገበየሁ፣ የባልቻ እና የሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን የጋራ ፍልሚያ፣ መስዋዕትነት እና ውህደት ውጤት እንጂ የነጠላ አካላት ስራ እንዳልሆኑ አብራርተዋል።

በየዘመናቱ የነበሩ ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች እና የአርሶ አደሮች አመጽም ለምሳሌ የጎጃም እና የባሌ ገበሬዎች አመጽ በየአካባቢው የነበረውን ተመሳሳይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ አብሮ የመኖር፣ የመጋመድ እና የማደግ ታሪካዊ ባህሪ በሁለቱ ብሔሮች መካከል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ በሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል በስፋት የሚገኝና የሀገሪቱ የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review