AMN – ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው እንዳሰፈሩት፤ የዘመነ መሰረተ ልማት እና አገልግሎት ለዘመናዊቷ ከተማ በሚል መሪ ሃሳብ በጎተራ፣ ቦሌ፣ የካ እና ቀበና አካባቢዎች የተገነቡ አራት ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣ ተርሚናሎች እና ገበያ ማዕከላት በይፋ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
እነዚህ አዳዲስ መሰረተ ልማቶች የትራፊክ መጨናነቅን የሚያቃልሉ፣ የትራንስፖርት ሥርዓትን የሚያሻሽሉ፣ ህዝቡን ከዝናብና ፀሐይ እንግልት የሚከላከሉ እንዲሁም በርካታ የሥራ እድሎችን የሚፈጥሩ ንፁህ እና የሰውን ክብር የሚመጥኑ ሆነው ተዘጋጅተዋል።
ማዕከላቱ በአንድ ጊዜ በርካታ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ካላቸው ዘመናዊ ማቆሚያዎችና የታክሲ እንዲሁም የአውቶቡስ ተርሚናሎች በተጨማሪ የአየር ብክለትን የሚከላከሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያዎችን አካተዋል።
እንዲሁም ሰፊ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎች፣ የንግድ ሱቆች፣ ካፍቴሪያና ሬስቶራንቶች፣ የልጆች መጫወቻና ማረፊያ ስፍራዎች፣ ምቹ የተሳፋሪ መጠበቂያዎች፣ የአስተዳደር እና የትኬት መቁረጫ ቴክኖሎጂዎች፣ አሳንሰሮች፣ ንፁህ መፀዳጃ ቤቶች እና የደህንነትና የአደጋ ቅድመ መከላከል ሥርዓቶች ሙሉ በሙሉ ተሟልተዋቸዋል።

ከለውጡ በፊት 3 ሺህ ብቻ የነበረው በአንድ ጊዜ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አቅም እና ምንም ያልነበረው የተርሚናል አገልግሎት፣ በአሁኑ ጊዜ በጥራትና በፍጥነት በተከናወኑ ሥራዎች ከ170 ሺህ በላይ ማድረስ ተችሏል።
የከተማ አስተዳደሩ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የገባውን ቃል በተጨባጭ በመፈጸም ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እንደሚገባትና በቀጣይም ከተሰሩ ሥራዎች በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ የዛሬዎቹ ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ ለተሳተፉ የዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ አመራሮችና ሠራተኞች፣ የትራንስፖርት ቢሮ አመራሮች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እና በሂደቱ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡