በወሰንና ማንነት ጥያቄዎች ላይ ሚዛናዊና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እየተሰራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

የፌደራል መንግሥት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሀገሪቱ በሚነሱ የፖለቲካ እና የልማት ጥያቄዎች ላይ በርካታ መፍትሔዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን ጨምሮ ዘላቂ መፍትሔ የሚሹ የፖለቲካ ጉዳዮች በሕጋዊ ውይይት እንጂ ለአጭር ጊዜ እፎይታ ተብለው በሚወሰኑ ጊዜያዊ ውሳኔዎች ሊመለሱ እንደማይችሉ አስታውቀዋል።

በሕገ-መንግሥቱ፣ በባንዲራ፣ በአንቀጽ 39 እና በወሰን ጉዳዮች ላይ የሚነሱ የፖለቲካ ጥያቄዎች ረጅም ጊዜ የሚወስዱና የበርካታ ወገኖችን ተሳትፎ የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ በአንድ አካባቢ፣ ክልል ወይም ፓርቲ ውሳኔ ብቻ የሚመለሱ እንዳልሆኑ አስረድተዋል።

እነዚህን ውስብስብ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በተለይም በወልቃይት ጉዳይ ለአጭር ጊዜ ደስታና እፎይታ ተብሎ ለአንዱ ወገን ብቻ ያደላ ውሳኔ መስጠት፣ ነገ ተመልሶ ግጭት የሚጋብዝ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የወልቃይት ጥያቄ ሁለቱንም ክልሎችና ሕዝቦች ያሳተፈ፣ በውይይትና በሕገ-መንግሥታዊ አሠራር ወይም በሪፈረንደም የተረጋገጠ ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ሰላም ማምጣት እንደማይቻል አብራርተዋል።

ከረጅም ጊዜ ምላሽ ከሚሹ ጉዳዮች ባሻገር ቀደም ሲል የነበረውን “ባለቤት እና አጋር” የሚል የፖለቲካ ክፍፍል በማስወገድ በፓርቲና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ፍትሐዊ ተሳትፎ እንዲኖር መደረጉን ተናግረዋል።

ክልሎች በፌደራል ተቋማት ፍትሐዊ ውክልና እንዲኖራቸውና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በካቢኔና በፓርላማ እንዲሳተፉ በማድረግ በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የመደመር መንግሥት በሀገር በቀል እውቀቶችና እሴቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቅኔን ለኮሙኒኬሽን፣ ደቦን ሀብትን አስተባብሮ ለመሥራት፣ ሽምግልናን ለእርቅ፣ እንዲሁም የገዳ ሥርዓትን ለተቋማት ግንባታና ለሥልጣን ክፍፍል እንደ መሠረት መጠቀማቸውን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማጠቃለያቸው፣ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ምላሽ ለማግኘት ጊዜና ትዕግሥት የሚጠይቁ በመሆናቸው ሕዝቡ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ሂደቱን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በበረከት ጌታቸው

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review