አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ የቀጠለው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አብዮት

You are currently viewing አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ የቀጠለው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አብዮት

AMN – ሐምሌ 26/2018 ዓ.ም

የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስጋት በደቀነበት እና የምግብ ዋስትና ፣ የውሃ እጥረት እንዲሁም የተፈጥሮ መመናመን ሀገራትን እየተፈታተነ ባለበት በዚህ ዘመን ፣ ኢትዮጵያ ታላቅ የሆነ አካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ እያከናወነች ትገኛለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በ2011 ዓ.ም ይፋ የተደረገው “የአረንጓዴ አሻራ” መርሃ ግብር የሀገሪቱን የመሬት መራቆት ለመግታት እና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት እየተከናወነ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ መርሃ ግብር ከዕቅድ በላይ የሆኑ ታሪካዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አድናቆትን አትርፏል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ 48 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

በአንድ ዕለት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል የተቻለባቸው ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳቡ የህዝብ ንቅናቄዎችም የኢትዮጵያ ህዝብ ለአካባቢ ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳዩ ናቸው።

ህፃናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያን፣ የሃይማኖት አባቶች እና የመንግስት አካላት በጋራ በመውጣት አረንጓዴ አካባቢን የማበልጸግ ባህል አዳብረዋል።

ከ2011ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ጀምበር የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ ነው የቀጠለው። በ2011ዓ.ም ከ353 ሚሊዮን በላይ ፣ በ2015ዓ.ም ከ566 ሚሊዮን በላይ ፣ በ2016 ዓ.ም ከ615 ሚሊዮን በላይ ፣ በ2017ዓ.ም 714 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ አሻራ አስመዝግበዋል።

ዘንድሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ ባደረጉት መሰረት 800 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ኢትዮጵያውያን ተዘጋጅተዋል። ሐምሌ 27 ዕለተ ሰኞ ኢትዮጵያውያን ዳግም ታሪክ የሚያስመዘግቡባት ዕለት ትሆናለች።

የተተከሉት ችግኞች ክትትል እና እንክብካቤ እየተደረገባቸው የጽድቀት ምጣኔያቸው ከፍ በማለቱ ፣ ቀደም ሲል ተራቁተው የነበሩ ተራሮችና ኮረብቶች አሁን በለምለም እጸዋት ተሸፍነዋል። ይህም የመሬት መሸርሸርን ከመቀነስ ባሻገር የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጎለብትና የውሃ ምንጮች እንዲያንሰራሩ አድርጓል።

በየዓመቱ ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፍራፍሬ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ ያሉ ፣ የቡና እና የከብት መኖ ተክሎች የተካተቱ መሆኑ፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ተጨማሪ ገቢ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዜጎችን አስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ የለወጠ ታላቅ ንቅናቄ ለመሆን በቅቷል። ህዝቡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የመንከባከብ፣ የማጽደቅ እና የደን ልማቶችን የመጠበቅ ባህልን እንዲያዳብር አድርጓል።

በአረንጓዴ አሻራ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ለመጪው ትውልድ አረንጓዴ ኢትዮጵያን ለማስረከብ የሚያስችል አስተማማኝ መሰረት ሆኖም ያገልግላል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review