ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ዕድልን፣ በጉድለት ውስጥ አቅምን ፈልጋ የማግኘት ታሪካዊ ጽናት አላት – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ዕድልን፣ በጉድለት ውስጥ አቅምን ፈልጋ የማግኘት ታሪካዊ ጽናት አላት – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ጳጉሜን 1/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ዕድልን፣ በጉድለት ውስጥ አቅምን፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተስፋን ፈልጋ የማግኘት ታሪካዊ ጽናት አላት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ማንሠራራት፡ ከዕድል ወደ እመርታ፣ ከእመርታ ወደ ከፍታ በሚል መለዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ማንሠራራት የሚያመላክተውን የጳጉሜን 1 የእመርታ ቀን አክብረናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቆመችበት ከተነሣች እና ከተንቀሳቀሰች ቆይታለች፤ አሁን በሙሉ አቅሟ ወደ ላቀ ከፍታ እያንሠራራች ያለችበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ዕድልን፣ በጉድለት ውስጥ አቅምን፣ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ተስፋን ፈልጋ የማግኘት ታሪካዊ ጽናት አላት ብለዋል።

የዛሬው እመርታችን የትናንት ቁርጠኝነታችን ፍሬ ነው፤ የነገው ከፍታችን ደግሞ የዛሬ ትጋታችን ውጤት ይሆናል።

በግብርና የምግብ ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን፣ በኢንዱስትሪ ከሸማችነት ወደ አምራችነት እየተሸጋገረን፣ በማዕድን ዘርፍ የተፈጥሮ ፀጋችንን በዕሴት ጭማሪ ወደ ሀገራዊ ሀብት እየቀየርን እንገኛለን።

በዲጂታል ለውጥና የአገልግሎት አሠራር ዘመናዊነትም ጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት ጥለናል። ይህ ጉዞ ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል የሚያሸጋግር የኢትዮጵያ የእመርታ ጉዞ ነው።

ለእኛ አምራችነት ዕሳቤም፣ ስልትም፣ ግብም ነው። ሥራችን፣ ንግግራችን እና ፕሮጀክቶቻችን ሁሉ ዕሴት የሚጨምሩና ምርት የሚያስገኙ መሆን አለባቸው።

ዛሬ ያገኘነውን እመርታ ወደ ነገ ከፍታ ለመቀየር የበለጠ መሥራት፣ የበለጠ ማምረት፣ የበለጠ መፍጠር እና መፍጠን ይጠበቅብናል። በወጣቶቻችን እውቀት፣ በአምራቾቻችን ቁርጠኝነት እና በሕዝባችን አቅም ራሷን የቻለችና የማትበገር ኢትዮጵያን እንገነባለን።

የኢትዮጵያ ማንሠራራት ይቀጥላል፤ እመርታው ይፋጠናል።የኢትዮጵያ ከፍታ አይቀርም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review