የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የአረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ሚና አለው-ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ

You are currently viewing የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የአረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ሚና አለው-ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ

AMN ሐምሌ 27/2018

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የአረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ሚና አለው ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በአዳማ ከተማ አዋሽ መልካሣ ወረዳ ዋቄ ሚዓ ቀበሌ ተገኝተው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

በእለቱ የጠቅላይ ምክር ቤቱ አመራር፣ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስመንት ምክትል ኮሚሽነሮችን ጨምሮ የተለያዩ ዕንግዶች በስፍራው በመገኘት ችግኝ ተክለዋል።

ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በወቅቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል የአረንጓዴ አሻራ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ችግኝ ብቻ ሳይሆን በጋራ ሆነን አንድነት፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና አብሮነትን ነው የምንተክለው ብለዋል ሼህ ኢብራሂም።

የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለመጠበቅ ችግኝ መትከልና የተተከሉትን መንከባከብ ከትውልድ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በበኩላቸው፤የዛሬው ቀን የኢትዮጵያዊያን ፅናትና ቁርጠኝነት በዓለም አደባባይ የሚረጋገጥበት ቀን ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት የሚተከሉት 800 ሚሊዮን ችግኞች የካርበን ልቀትን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቋቋም ወሳኝ ሚና አላቸው ነው ያሉት።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ እንደገለፁት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም፣የግብርና ምርትና ምርታማነት ለመጨመርና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከግብ ለማድረስ በተደረገው ጥረት አዳማ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ናት ብለዋል።

በአዳማ በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን በዛሬው ዕለት በአብዛኛው ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች በስፋት ይተከላሉ ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review