AMN – ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከተማ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማስፋትና መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መቆየቷን የከተማዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ገለጹ።
“በስፖርት የዳበረ አካል፥ በምክክር የሚፀና ሀገር” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መጠናቀቁን በማስመልከት በቦሌ ክ/ከተማ 24 ሜዳ የብዙኅን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል።
ከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች እየሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አሰግደው ፤ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋት የተከናወነውን ስራ በማሳያነት አስቀምጠዋል።

በተቀየረችው አዲስ አበባና ባለማቻቸው ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ላይ መገልገል የሚችል ትውልድም ተፈጥሯል ብለዋል።
ኃላፊው አክለው፤ ለአዲስ አበባ የሚገባትን የስፖርት አይነቶች በማምጣትና እስካሁን የነበሩትንም በማጠናከርና በመደገፍ ወደ ውጤት እንዲሸጋገሩ የሚከናወነው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አደፍርስ ኮራ በበኩላቸው፤ በስፖርት የታነፀና አካሉ የዳበረ ዜጋ ለሀገር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ ይህ እንዲሳካ ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ቦሌ ክፍለ ከተማም ለነዋሪዎች ምቹ የእንቅስቃሴ ማድረጊያ ምቹ ስፍራዎችን የመለየትና የመገንባት ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።
በ24 ሜዳ በተካሄደው የብዙኅን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሃ ግብር ላይ የከተማና የክፍለ ከተማው የስራ ኃላፊዎች፣ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች እና በአጠቃላይ የስፖርት ማኅበረሰቡ የተሳተፈበት ነው።
በበላይሁን ፍስሃ