ተፈጥሯዊ ተጽዕኖን ለመከላከልና የአካባቢን ደህንነት ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ከህፃናት እስከ አዛውንት፣ ከመንግስታዊ እስከ ግል ተቋማት፤ መላው የማህበረሰብ ክፍል ችግኞችን በመትከል ያሳየው ደማቅ ተሳትፎ የዘመቻውን እቅድ ከታሰበው በላይ እውን እንደሚያደርገው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መላው የከተማዋ ነዋሪ፣ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ቦታዎች ችግኞችን በመትከል ላይ ይገኛሉ።

የመንግስትና የግል ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ልዩ ልዩ ኩባንያዎች ባሏቸው ክፍት ቦታዎች ሁሉ ችግኝ በመትከል ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ይህም ህዝባዊ ንቅናቄ ከታቀደው ግብ በላይ በላቀ ውጤት እንደሚጠናቀቅ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉት ችግኞች የሀገሪቱን ብልጽግና፣ የነገዋን ልምላሜ እና ለተኪው ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ተስፋን የሚያመላክቱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ለጎርፍ አደጋና ለአየር መዛባት ተጋላጭነቱ እየጨመረ በመምጣቱ፣ ይህንን ተፈጥሯዊ ተጽዕኖ ለመከላከልና የአካባቢን ደህንነት ለመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ ስራው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ችግኝ ከመትከል ባለፈ የተተከሉትን በእንክብካቤ ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የተተከሉ ችግኞች እንዳናበላሸው፣ አላግባብ እንዳንቆርጠው ወይም ሌሎች ሲያበላሹም መከላከል እንደሚገባ አደራ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የጋራ ድካማችንና የጋራ ጥቅማችን ውጤት በመሆኑ፣ በጋራ መንከባከብና መጠበቅ ከሁላችንም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ህፃናት፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችና ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን ይህንን ተስፋ የመትከል ስራ በላቀ ኃላፊነት ስሜት በማከናወናቸው ምስጋናቸውን አቅርበው፣ መርሃ ግብሩ በታላቅ ድል እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review