AMN – ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬም በጋራ ሆነን ሌላ ታላቅ ታሪክ ፅፈናል ፤ ተስፋችንንም ተክለናል ሲሉ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፤ በከተማችን አዲስ አበባ “ተስፋን እንትከል!” በሚል መሪ ቃል በአንድ ጀንበር ሲከናወን የዋለውን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እጅግ ደማቅ በሆነ ነዋሪዎቻችን የነቂስ በመውጣት ፣በሚያስደንቅ ርብርብ ከዕቅዳችን በላይ 1.5 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሌላ አዲስ ታሪክ ፅፈናል፣ ሌላ አዲስ ድል አሳክተናል ብለዋል።
በእርግጥም ስንተባበር እንችላለን ያሉት ከንቲባዋ ሁላችንም በአንድነት ተግተን ስንሰራ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር አሻራ እናኖራለን፤ የማይነጥፍ ምንዳም እናኖራለን ነው ያሉት።

ይህ ታላቅ ስኬት እውን ይሆን ዘንድ ከማለዳው ጀምሮ ላደረጋችሁት የማይታክት ጥረት፣ ላሳያችሁት አስደናቂ አብሮነት እና የባለቤትነት ስሜት አሻራችሁን ላኖራችሁ የከተማችን ነዋሪዎች እና ላስተባበራችሁ አመራሮቻችን በከተማዋ አስተዳደር ስም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡