ካሰበችው በላይ የማድረግ ዐቅም ያላት ኢትዮጵያ

AMN- ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

ካሰበችው በላይ የማድረግ ዐቅም ያላት ኢትዮጵያ ዛሬ በአንድ ጀምበር 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞችን ተክላለች፡፡

በየዓመቱ አዳዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገብ የታታሪ ሕዝብ፤ የተደራጀ እና ፍሰቱን የጠበቀ አመራር ሰጭነት ውጤት ሲሆን ዛሬ ለራስ ሳይሆን ለትውልድ የተሰጠ ታላቅ ዕለት ነበር፡፡

ይህን ከሚያስረዱልን ሠበዞች መካከል አንዱ ኢትዮጵውያን የግል ጉዳያቸውን ሰርዘው ቅድሚያ ለሀገሬ ጥሪ ማለታቸው እና ነገን ዛሬ ሲገነቡ መዋላቸው ነው፡፡

በመላ ሀገሪቱ 800 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ተወጥኖ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በትጋት ሲከናወን ውሎ 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል በስኬት ተቋጭቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን በራስ ተነሳሽነት ለተሻለ ነገ ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሐሳብ በድግግሞሽ ሲተክሉ በመዋላቸው የሀገራቸውን ስም እንደገና በክብር ማስጠራት ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ የሚሳናቸው እንደሌለ በተደጋጋሚ ዐሳይተዋል፤ ዛሬም በአረንጓዴ ዐሻራ ማኖር መስክ ሌላ ድል አስመዝግበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የዕለቱ የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ ዛሬ ያሳካነውን ድል ብዙዎች ይመኙት ይሆናል እንጅ አያሳኩትም ብለዋል፡፡

ዛሬ ካቀድነው በላይ በአንድ ጀምበር 805 ነጥብ 3 ሚሊየን ችግኝ በመትከላችን፤ ኢትዮጵያ የዳበረ የማድረግ ዐቅም ዝግጁነት እንዳላት ደጋግማ ዐሳይታለች ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማም 1 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ግብ ተጥሎ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች በተደረገ የተናበበና የተቀናጀ ርብርብ ከታቀደው በላይ መፈጸም ተችሏል፡፡

ተከላው እየተከናወነ በነበረበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ እንበርታ! ከተማችንን በአብሮነት እናልብስ! እያሉ ሲያበረታቱ ነበር፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች የጀመርነውን እስከመጨረሻው ሠዓት ድረስ ርብርባችንን በማስቀጠል፤ የከተማችንን ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ ዐሻራ ማኖራችንን እንቀጥል እያሉ ሲያተጉ ውለዋል፡፡

ይህን የሚያደርጉት እርሳቸውም የሚጠበቅባቸውን በማድረግ እና አረንጓዴ ዐሻራቸውን በማኖር ጭምር ሲሆን ይህ ማበረታቻም ዐቅም እየሆነ ድካምን እያስረሳ እንደ ከተማ ከታቀደው በላይ በተሳካ ሁኔታ መፈጸም አስችሏል፡፡

ከንቲባ አዳነች በሰጡት ማብራሪያም፤ ለአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 176 ቦታዎች ተለይተው ተከላ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

የችግኞችን የጽድቀት መጠን በሚጨምር መልኩ በባለሙያ እየታገዘ መከናወኑን በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ለአዲስ አበባ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ከንቲባ አዳነች እንዳሉት የሚተከለው ምግብ፣ ጥላ እና ውበት ነው።

ወዲህ ደግሞ ችግኝ እየተተከለ ያለው ነገ በዓየር መዛባት ምክንያት የሚመጣውን የብክለት፣ የጤና ችግር፣ የጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ነው።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በችግኝ ተከላው እንዳሳዩት ብርታት ችግኞችን በመንከባከብም ሊደግሙት እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አደራ ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ አዲስ አበባ በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ካቀደችው በላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን መትከሏን ተከትሎ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእንኳን ደስአላችሁ የመልካም ምኞትና የምሥጋና መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፤ ነዋሪዎቻችን በነቂስ በመውጣት በሚያስደንቅ ርብርብ ከዕቅዳችን በላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ሌላ አዲስ ታሪክ ፅፈናል፤ ሌላ አዲስ ድል አሳክተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በእርግጥም ስንተባበር እንችላለን! ሁላችንም በአንድነት ተግተን ስንሠራ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚሻገር ዐሻራ እናኖራለን፤ የማይነጥፍ ምንዳም እናኖራለን ብለዋል።

የተጠናቀቀው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር እንጅ፤ የክረምቱ ወቅት ችግኝ ተከላ እንዳልሆነ በመገንዘብ አረንጓዴ ዐሻራ የማኖር ጥረትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ እንመክራለን፡፡

በዮሐንስ ደርበው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review