የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር – ከህዳሴው ግድብ እስከ አህጉሪቱ ግዙፍ ኤርፖርት

You are currently viewing የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር – ከህዳሴው ግድብ እስከ አህጉሪቱ ግዙፍ ኤርፖርት

AMN- ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም

ሲኤንኤን “ኮኔክቲንግ አፍሪካ” ዝግጅቱ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሽግግር እና የወደፊት የልማት ምኞቶች የሚያሳይ ሰፊ ዘገባ አቅርቧል።

በታዋቂዋ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሩባዲሪ የቀረበው ይህ ዘገባ፤ ሀገሪቱ ከቡና ኤክስፖርት ባሻገር የተለያዩ ግዙፍ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመክፈት ላይ እንደምትገኝ አብራርቷል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ፣ የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ከ50 በመቶ በላይ እንደሚያሳድግ አንስቷል።

ከ4.2 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተው ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ እና የሀገር ውስጥ ቦንድ የተሸፈነ ነው።

ቀጣናዊ ትስስርን ከማጠናከር አንፃር ለኬንያ፣ ጂቡቲ እና ሱዳን ኃይል ማቅረብ የተጀመረ ሲሆን፣ ወደ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ለማስፋፋት እየተሰራ እንደሚገኝም ዘገባው አትቷል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2024-2025 በጀት ዓመት መጨረሻ የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በመድረስ ቡናን በመበለጥ አንደኛ የኤክስፖርት ገቢ ማግኘት መጀመሯንም ገልጿል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ ፕሮጀክት በዓመት 9 ቶን ወርቅ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ በዓመት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጀው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በአፍሪካ ትልቁ የግንባታ ቦታዎች አንዱ ነው።

በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እና 4 ሚሊዮን ቶን ካርጎ የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረውም ነው ዘገባው ያተተው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ ኤርፖርቱ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ለማስፈጸም እና አህጉራዊ ትስስርን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል።

ከቱሪዝም እና የኢኮ-ቱሪዝም አቅም ማደግ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ ትልቅ እምርታ እያስመዘገበች እንደምትገኝ የጠቀሰው ዘገባው፣ በዩኔስኮ የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፡ እንደ የኢትዮጵያ ተኩላ እና ኒያላ ያሉ ዝርያዎች መኖሪያ ሲሆን፣ ለዓለም አቀፍ እና ለአፍሪካውያን ጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡለት እንደሚገኝ አመላክቷል።

የቪዛ ማሻሻያን በተመለከተም፣ ለአፍሪካውያን እና ለሌሎች ጎብኚዎች የ7 ቀን ነፃ የመቆያ የቱሪዝም ፓኬጆችን በመስጠት የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚ ሞተር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዘገባው ገልጿል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review