ሆስፒታሉ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን ነጻ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነዉ

You are currently viewing ሆስፒታሉ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን ነጻ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነዉ

AMN – ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ3 ሺህ በላይ ዜጎችን ነጻ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል፡፡

ሰዎች ሃሳብና ጉልበታቸውን እንዲሁም ገንዘባቸውን ተጠቅመው በራስ ተነሳሽነት የሚሰሩት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እንደ ሃገር ብሎም እንደ አዲስ አበባ ከተማ ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡

አገልግሎቱ በተቋማት ደረጃም በስፋት እየተተገበረ ሲሆን ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም በክረምቱ “እሺ ለበጎ ተግባር” በሚል መሪ ሀሳብ በተመረጡ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ነጻ ህክምና እና የጤና ምርመራ እያካሄደ ነው።

በዚህ መልካም ተግባር ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን የሚያገኙ ሲሆን 70 የጤና ባለሙያዎችም እየተሳተፉ ይገኛል፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ህክምና ሃኪም ዶክተር ኢዩኤል ተስፋዬ፤ በዚህ ነጻ የህክምና አገልግሎት ብዙ አይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የአጥንት፣ የቆዳ፣ የነርቭ፣ የህፃናት፣ የውስጥ ደዌ፣ የጥርስ ህክምና በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

የጤና አገልግሎት እና የጤና ምክር በነጻ መሰጡቱ የጤና ሁኔታቸውን በጊዜ ለማወቅ እንደሚረዳቸውና ትልቅም ድጋፍ ስለመሆኑ ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

የነጻ ህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ አቶ ታመነ ከፈኒ፤ ነጻ የህክምና አገልግሎቱ በበጎነት በየአካባቢያቸው መሰጡቱ ለገንዘብ ወጪ እንዳይዳረጉ ከማድረግ ባለፈ በቅርብ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ የነጻ ህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ወ/ሮ ብዙአየሁ መኩሪያው በበኩላቸው፤ በነጻ የህክምና አገልግሎቱ ጥሩ እንክብካቤ እያገኘን ነው ብለዋል፡፡

ነጻ የህክምና አገልግሎቱ ብዙ ድካም እና እንግልት የቀነሰ መሆኑን በመግለጽ አገልግሎቱ እንዲቀጥል የጠየቁት ደግሞ አቶ ሲራጅ አወል ናቸው፡፡

በለሚኩራ ክፍለ ከተማ እንደዚህ አይነት የበጎነት ተግባርን ለማጠናከር በጥረት እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የክፍለ ከተማው ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ልመንህ ምህረቱ ናቸዉ።

ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚሰጠው ይህ የበጎነት ተግባር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review