AMN – ነሐሴ 22/2018 ዓ.ም

የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን አቅም በማጠናከር ተወዳዳሪና ጥራት ያለው ትምህርት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስገኙ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ( ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ትምህርት በቀለም ትምህርት ብቻ ሳይወሰን ተማሪዎችን በሙያና በክህሎት ጭምር መቅረጽ እንደሚገባው ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል አጥጋቢ ውጤት የማያመጡ የነበሩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ አሁን ላይ ከ20 በመቶ በላይ ተማሪዎችን ማሳለፍ መቻላቸው ትልቅ ለውጥ መሆኑን አንስተዋል።
ይህን የተመዘገበ ስኬት ለማስቀጠልና የበለጠ ለማጠናከር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው የሰመር ካምፕ መርሃ ግብር ትልቅ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

በዚህም የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በልዩ ትኩረት እየተደገፉ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በክፍል ደረጃ የመጀመሪያዎቹን 30 ተማሪዎች በመምረጥ የተጠናከረ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በማኅበረሰቡ ዘንድ በመንግሥትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የተሳሳቱ አመለካከቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ዘላለም ሙላቱ( ዶ/ር) ፤ ወላጅ በቅርበት የተከታተለውና የተቆጣጠረው ተማሪ የበየትኛውም ትምህርት ቤት ቢማር ውጤታማ መሆኑ እንደማይቀር አስገንዝበዋል።
ወላጅ ያልተከታተለውንና ያልተቆጣጠረውን ተማሪ ትምህርት ቤቱ ብቻውን ምንም ሊያደርግለት አይችልም ሲሉ ያስገነዘቡት ኃላፊው ፤ የኅብረተሰቡንና የወላጆችን ሚና አፅንኦት ሰጥተዋል።
በአሁኑ ወቅት ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ሊነጥሏቸው የሚችሉ ዘርፈ ብዙ የቴክኖሎጂ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖዎች በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ አመላክተዋል።
ወላጆች የልጆቻቸውን የቤት ውስጥ ቆይታ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሁኔታን በንቃት ሊከታተሉና ሊቆጣጠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ