AMN- ሐምሌ 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አነስተኛ ንግዶችን ለማበረታታት፣ የግብር ጫና እንዳይደርስባቸውና ትርፋማነታቸውን በማጎልበት ወደ ቀጣይ ደረጃ እንዲሸጋገሩ በቁርጠኛነት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ቢሮው ባለፉት ሁለት ዓመታት ፍትሐዊ የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለመዘርጋት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን ማከናወኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ገልጿል።
በከተማዋ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች፣ በኪራይ እና በራይድ ትራንስፖርት የተሰማሩ አጠቃላይ 456 ሺህ 433 የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም 9.2 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።
ይህ የግብር መጠን በመንግስት እና በግል ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ ተቀጣሪ ደመወዝተኞች ከሚሰበሰበው ዓመታዊ የግብር ገቢ ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተመላክቷል።
ይህም የከተማ አስተዳደሩ አነስተኛ ነጋዴዎችን ለመደገፍና የግብር ጫናውን ለማቃለል ካለው ቁርጠኝነት የመነጨ ነው።
የ2018 የግብር ዘመንን በተመለከተ አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች በተዘረጋው የኦንላይን የክፍያ ስርዓት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
በዚህም መሰረት እስከ ሐምሌ 25 ቀን ድረስ አጭር የጽሁፍ መልዕክት የደረሳቸው ግብር ከፋዮች ከቅጣት እና ወለድ ራሳቸውን ጠብቀው እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ ጥሪ ቀርቧል።
በተለያዩ ምክንያቶች መልዕክት ያልደረሳቸው ወይም ከሐምሌ 25 በኋላ መልዕክት የተላከላቸው ግብር ከፋዮች ወደ ቅጣት የማይገቡ በመሆኑ እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ መክፈል የሚችሉ ሲሆን፣ መልዕክት ያልተላከላቸው አካላትም በትዕግስት እንዲጠባበቁ ቢሮው አሳስቧል።
ለግብር ከፋዮች የተላከው የገንዘብ መጠን ቅድመ ታክስን ተቀናሽ በማድረግ የተሰላ መሆኑም ተገልጿል።
በሌላ በኩል መልዕክት ከተላከለት በኋላ “ግብር በዛብኝ” የሚል ቅሬታ ላለው ማንኛውም ግብር ከፋይ ፈጣን የቅሬታ አፈታት ስርዓት ተዘርግቷል።
በዚህም መሰረት ቅሬታ ያለው አካል በወረዳ ደረጃ ማመልከት የሚችል ሲሆን፤ መረጃው ለክፍለ ከተማ ተላልፎ በክፍለ ከተማው በተደራጀ የቀን ገቢ ገማች አማካኝነት ድጋሚ ግምት በማካሄድ ቅሬታዎች እንዲስተካከሉ አሰራር መመቻቸቱ ተገልጿል።
በ2019 በጀት ዓመት እንደ ከተማ 502.27 ቢሊየን፣ በገቢዎች ቢሮ 380 ቢሊየን ብር ገቢን በፍትሃዊነት ለመሠብሰብ መታቀዱን ቢሮው ለኤ ም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡