በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ እየተመራ ያለው ማስተካከልን፣ ማዘመንን፣ ማሣመርንና ማመቻቸትን ገዥ መርሕ በማድረግ ነው፡፡

ማስተካከል፤ ቀድሞ የነበሩትን መንገዶችና ዐደባባዮች፣ የመንገድ ላይ መብራቶችና የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የቴሌ፣ የውኃና የመብራት የአገልግሎት መሥመሮች ማስተካከልን ነው፡፡
ማዘመን፤ በዚህ ዘመን የሚሠራን ሥራ ከዲጂታል ኢትዮጵያ ርዕይና ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር ማስተሣሠርን ነው፡፡ ለምሳሌ የእሳት አደጋ ቢነሳ ውኃ ለመቅዳት የሚያስችል መሠረተ ልማት በየአካባቢው በበቂ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት በመንገዶች ላይ ሠርተናል፡፡
ማሣመር፤ የምንሠራቸው ሥራዎች ውበታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ንጽሕናንና ውበትን በማስተሣሠር ከተማችንን ጽዱና ውብ የሚያደርጉ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ዛፎችና ሣሮች ተተክለዋል፡፡ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ የመንገድ ላይ የአጥር ግንቦችን በማፍረስና ደረጃ በመስጠት ቤቶችና መንገዶች እንዲጣጣሙ ተደርጓል፡፡ የተደበላለቀ የነበረው የሕንጻዎች ቀለም የተግባባ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ከዓይን ባለፈም የአየር ንብረት ለውጥን በማስተካከል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው አረንጓዴና የቆሻሻ አወጋገድ አስተዳደር ተዘርግቷል፡፡ አዲስ አበባ ከግራጫ ጠርዞቿ እንዲሁም ከባዕድ ጠረኗ እየተላቀቀች ነው፡፡
ማመቻቸት፤ አካባቢን ለነዋሪዎች፣ ለመንገደኞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ወዘተ. ምቹ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመንገድ ላይ ማረፊያዎች ሠርተናል፡፡ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን በዘመናዊ መልኩ ሠርተናል፡፡ መንገዶችን ለአካል ጉዳተኞች፣ ሠፈሮችን ደግሞ ለሕጻናት ምቹ አድርገናል፡፡ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የፍሳሽ፣ የቴሌ መሥመሮች ለጥገና ምቹ ተደርገዋል፡፡
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ ከ242 – 243