AMN – መስከረም 13/2019 ዓ.ም
በአደባባይ የሚከበሩትን የመስቀለ ደመራና የኢሬቻ በዓላትን ተከትሎ ለጎብኝዎች አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን የቱሪዝም ፕሮሞሽንና ልማት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ባለፈው ዓመት ከ350 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች የአደባባይ በዓላቱን መታደማቸውን ገልፀዋል።
ከቀናት በኋላ በሚከበረው የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላትም ከአምናው የበለጠ ጎብኚ ወደ ከተማዋ ይገባል ተብሎ አንደሚገመት ጠቁመዋል።
በዚህም አገልግሎት ሰጪ የሆኑት ሆቴሎች ፣ የትራንስፖርት አሽከርካሪዎችና ሌሎችም ተቋማት የዋጋ ጭማሪ ሳያደርጉ እንግዶችን ማስተናገድ እንደሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት።
ይህን ለማድረግም ኮሚሽኑ ሰነድ በማዘጋጀት ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ቢኒያም ታዬ ተናግረዋል።
የመስቀል ደመራ በሚከበርበት መስቀል አደባባይና የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ሆራ ፊንፊኔ መሀል በሆነው በእስጢፋኖስ አካባቢም ጎብኝዎች ጠቃሚ መረጃዎችን የሚያገኙበት ጊዜዊ የመረጃ ማዕከል ከባለሙያ ጋር እንሚዘጋጅ ገልጸዋል።
ጊዜያዊ ማዕከሉ በሳለፍነው ዓመት ተሞክሮ ጥሩ ውጤት የታየበት በመሆኑ በቀጣይ ቀናትም ከበዓላቱ አንድ ቀን አስቀድሞና በበዓሉ እለት አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል።
በዮሐንስ አበበ