AMN – ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላፉት መልዕክት ፣ ዛሬ መርቀን አገልግሎት ያስጀመርነው የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የአየር መንገዳችን ደማቅ የስኬት ጉዞ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ዘመናዊ ተርሚናል ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያው ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ከተማዋን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ የሁለተኛው ትልቅ የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከልነት ሚና እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የላቀ ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከፍተኛ የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባው ይህ ደረጃውን የጠበቀ ተርሚናል ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብቶችን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በቀጥታና በምቾት ለማስተናገድ በዕጅጉ እንደሚረዳም ነው የገለጹት።

በተጨማሪም የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ፣ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና በትራንስፖርት ዘርፎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ባሕር ዳርን የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ሁነቶች ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ አቅምን ይፈጥራል ብለዋል።

ፕሮጀክቶችን አቅዶ መጀመር ፣ በጥራት ፈጽሞ ለህዝብ አገልግሎት ማብቃት የመደመር መንግሥት ባህልና መገለጫ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፣ ይህ የትጋትና የመፈጸም ጉዟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የውበት፣ የልምላሜና የፀዳል ተምሳሌት የሆነሽው ውቧ ባሕር ዳርና የአካባቢው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።