የኬንያዊው ተጓዥ ጋዜጠኛን ቀልብ የሳበው የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ

You are currently viewing የኬንያዊው ተጓዥ ጋዜጠኛን ቀልብ የሳበው የአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ

AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ ከዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ባለፈ፣ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን፤ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን እና የተጓዥ ጋዜጠኞችን ቀልብ በከፍተኛ ሁኔታ እየሳበች ትገኛለች።

አዲስ አበባን የጎበኘው የኬንያው ተጓዥ ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ ያደረገውን ቆይታና የታዘበውን አስደናቂ የኮሪደር ልማት፣ የጽዳትና የውበት ሥራዎች “አዲስ አበባ የአፍሪካ ዱባይ ሆናለች” በማለት ለዓለም አቀፍ ተከታዮቹ እያስተዋወቀ ይገኛል።

የኬንያው ተጓዥ ጋዜጠኛ ጉብኝቱን የጀመረው በአፍሪካ ግዙፍ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አካባቢን በማሳየት ሲሆን፣ በከተማዋ ሰማይ ስር የተገነባውን ስካይ ላይት ሆቴልንና አዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን የጎበኘው ጋዜጠኛው፣ አዲስ አበባን “ሳቢና ንጹህ የአፍሪካ ከተማ” ሲል ገልጿታል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ታቅደው ወደ ሥራ ከገቡት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የኮሪደር ልማት፣ የከተማዋን ገጽታ በአዲስ መልክ መቀየሩን ጋዜጠኛው በዘገባው ተንትኗል።

በተለይም ፒያሳ እና ካሳንቺስ ያሉ አካባቢዎች የቀደመ ታሪካቸውን ሳይለቁ፣ እሴት ተጨምሮባቸውና ለትውልድ በሚሻገር መልኩ መገንባታቸውን አድንቋል። ቀደም ሲል የመጥፎ ሽታና የበሽታ ምንጭ የነበሩ ወንዞች ጸድተውና ለምተው ለእግር ጉዞ፣ ለብስክሌትና ለመዝናኛ አመቺ ሆነው ማየቱ እጅግ እንዳስገረመውም ገልጿል።

በአድዋ ድል መታሰቢያ በመገኘት የኢትዮጵያን ያለመገዛት ታሪክ ለተከታዮቹ የዘገበው ጋዜጠኛው፣ ከተማዋ የታሪክ ብቻ ሳይሆን የቴክኖሎጂም ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ሳይጠቅስ አላለፈም።

የሳይንስ ሙዚየምንና የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት በመጎብኘትም፣ ለትውልድ ዕውቀትና ለወደፊት ራዕይ የተሰጠውን ትኩረት ተመልክቷል። ጋዜጠኛው በቆይታው የከተማዋን የዲጂታል አገልግሎት ቅልጥፍና በተግባር የታዘበ ሲሆን፣ የስማርት ባንክ የኤ ቲ ኤም አገልግሎትን ከመጠቀሙ ባለፈ፣ ወደ ማረፊያው ሲመለስ በዲጂታል ክፍያ ብስክሌት ተከራይቶ በኮሪደሩ ላይ እየነዳ መጓዙ አዲስ አበባ ለኑሮ ምን ያህል ምቹ እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ ነው።

በምሽት መብራቶች እንዲሁም በውሃ ትርዒቶች የተዋበችውን አዲስ አበባን ውበት እየተመለከተ” ውይ አዲስ አበባ! በእውነትም ውብ ናት” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

የኬንያዊው ጋዜጠኛው ጉብኝት አዲስ አበባ ለመላው አፍሪካ ኩራትና የብልጽግና ተምሳሌት መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዳግም ያበሰረ ሆኗል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review