ችግርን ወደ እድል በመቀየር ለትውልድ የሚሻገር ታላቅ ፕሮጀክት መገንባት ተችሏል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN – ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

ችግርን ወደ እድል በመቀየር ለትውልድ የሚተርፍ የላቀ ልማት ማከናወን መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል ምረቃ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ሀገራዊ ትብብር፣ ሰላም እና የውስጥ አንድነት ለአካባቢው ዘላቂ እድገት ወሳኝ መሆናቸውን ገለጸዋል።

አንድ ወገን የሚገነባውን ልማት ሌላው ወገን የሚያፈራርሰው ከሆነ ሀገርና ህዝብ ሊጠቀሙ እንደማይችሉ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀኙ ግራውን መቆንጠጥና ማሳረፍ ካልቻለ ያየናቸው ተስፋዎችና ሙከራዎች ሊበላሹ ይችላሉ ሲሉ አሳስበዋል።

የአዲሱን ተርሚናል ግንባታ በተመለከተ ማብራሪያቸው የቀደመው አሮጌ ተርሚናል በግጭት ምክንያት ጉዳት ከደረሰበት በኋላ ችግሩን ወደ መልካም እድል በመቀየር የተሻለ፣ የላቀና ለትውልድ የሚሻገር ዘመናዊ ተርሚናል መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

ባህር ዳር ከአፍሪካ ዋና ከተሞች ጋር የሚወዳደር ትልቅ የልማትና የቱሪዝም አቅም ያላት ከተማ መሆኗን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን አቅም እውን ለማድረግ ሰላም፣ ትጋትና በጋራ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑት የልማትና የሪፎርም ሥራዎች ጎን ለጎን የክልሉ አመራር ክልሉን የማስተዳደርና ውሳኔዎችን የመስጠት ሙሉ ስልጣን እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፤ እንተባበር፣ ባህር ዳርን እናልማ ፣ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ እንደ ጨዋ በንግግር እንጨቃጨቅ ፣ ጊዜ ግን እንዳያልፍብን እንጠንቀቅ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review