የባሕር ዳር ከተማ ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ

AMN- ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሕር ዳር ከተማ ገቢዋን በማሳደግ ራሷን እንድትችል ማድረግ እና ሰላምን ማረጋገጥ ለቀጣይ የልማት ስራዎች ማዕከላዊ ምሰሶ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ ተርሚናልን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው ፣ ይሁን እንጂ የከተማዋ የገቢ አቅም ከዕድገቷ ጋር ሊጣጣም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ባሕር ዳር፣በኢትዮጵያ ውስጥ ከቦሌ ቀጥሎ ትልቁ ተርሚናል አለ ፣ ትልቁ ድልድይ አለ ፣ ትላልቅ ሪዞርቶች ተገነቡ ፣ ስታዲየም እየአለቀ ነው ብንልም ዛሬ ባህር ዳር ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከተሞች ገቢዋ 7ኛ ደረጃ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማዋን ገቢ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የከተማዋ ገቢ ካልተሻሻለ የአስተዳደር ኃላፊዎች ከተማውን በዕይታ ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት ውስንነት እንደሚገጥመው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ዘላቂነት ለመጠበቅ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

ባሕር ዳርን ለጎብኚዎች እና ለባለሀብቶች ማራኪና ምቹ በማድረግ ሐብት የሚያፈሱበት ማዕከል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ከተማዋ ራሷን ችላ፣ በሂደትም እየለማች መሄድ እንድትችል መላው የከተማው ነዋሪዎች እና የክልሉ መንግሥት ከከንቲባው ጋር በመተባበር መረባረብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ባህር ዳር የሚገባትን የገቢ ልክ ማመንጨት እንድትችል ተጨማሪ እና የተቀናጁ ስራዎች ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review