AMN – ነሐሴ 1/2018 ዓ.ም
ብልፅግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ያገኘውን የህዝብ ውክልና ወደ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ለመቀየር እየሰራ እንደሚገኝ የፓርቲው ዋና ፅ/ቤት የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በዚሁ ወቅት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ጠንካራ ሀገር ለመገንባትና ዜጎችን ከድህነት ለማውጣት ዋናው መነሻ በርዕይ፣ በአመራር፣በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀትና በቁሳቁስ የበቃና ውጤታማ ፓርቲ መገንባት ነው።
ብልፅግና ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከህዝቡ ጋር ትብብርና ተሳትፎን መሰረት ያደረገ ጠንካራ ቁርኝት መፍጠሩን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት በፓርቲው መሪነት የተነደፉትና የተተገበሩት በርካታ ስትራቴጂዎች በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙና በየደረጃው ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማንቀሳቀስ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በተተገበሩ የግብርና ማሻሻያዎች ኢትዮጵያ የምግብ ሉዐላዊነቷን የማረጋገጥ ጉዞ መጀመሯን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ የስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አካባቢን የመንከባከብና የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅም መገንባቷን ጠቅሰዋል።
በከተሞች ልማትና ገጽታ ግንባታ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቷ ከተሞች ዘመናዊና የከተማ ደረጃን የሚያሻሽሉ የኮሪደርና የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
ብልፅግና ፓርቲ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከህዝብ ያገኘውን አዲስ የህዝብ ውክልና መነሻ በማድረግ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገባቸውን የማኒፌስቶ ሃሳቦች ወደ ዝርዝር የድርጊት መርሃ ግብሮች በመቀየር ላይ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይ አምስት ዓመታት በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች እንደሚተገበሩ ጠቅሰው፤ ዜጎችን ከድህነት በማውጣት ሀገሪቷንና ማህበረሰቡን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማሸጋገር ይሰራል ብለዋል።
በብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ግብርናን፣ማኑፋክቸሪንግን፣ ቱሪዝምን፣ ማዕድንና ዲጂታል ኢኮኖሚን በማስፋፋት በቤተሰብና በግለሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ በማረጋጋት፣በትምህርት፣በጤና፣ በባህልና በቋንቋ እድገት ላይ ትኩረት በማድረግ ማህበራዊ ልማትን ለማፋጠን እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የህዝቦችን አንድነት፣ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት የሚያረጋግጡ ታላላቅ የወል ግንባታ ስራዎች እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ምክክር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን በመሳተፍ ላይ የሚገኙበት አካታች ሀገራዊ የምክክር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆኑንም ከፓርቲው ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡