AMN- ሰኔ 05/2018 ዓ.ም
የማኅበራዊ ሳይንስና የሥነ-ባህሪ ምሁራን እንደሚገልጹት ፣ በጎ ተግባር የሰውን ልጅ ጭንቀት የሚቀንስ፣ ደስታን የሚጨምርና የእርካታ ስሜትን የሚፈጥር ውስጣዊ አበረታች ሂደት ነው።
የስነ-ምግባር፣ የፍልስፍና እና የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎችም በጎ ተግባር በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ መተማመንን፣ ትብብርንና ሰላምን የሚገነባ ማኅበራዊ ካፒታል ሲሉ ይገልጹታል።
በተመሳሳይ የዓለም ባንክ የሰብአዊ ልማት ሪፖርቶችም በጎ ተግባር መንግሥት ብቻውን ሊሸፍናቸው የማይችላቸውን እንደ ድህነት መቀነስና ትምህርትን ተደራሽ ማድረግ ያሉ ማኅበራዊ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚደረግ የግል ዘርፍ ያልተማከለ የሀብት ክፍፍል መሆኑን ያመላክታሉ።
ምሁራኑ በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ያስቀመጡት ይህ የደግነትና የሰብአዊነት መርህ፣ በተግባር ሲተረጎም ደግሞ የማኅበረሰባዊ ትስስር ዋነኛ ምሰሶ ይሆናል።

በተለይም እንደ አዲስ አበባ ባሉ ፈጣን እድገትና ማኅበራዊ ለውጦች ውስጥ በሚያልፉ ታላላቅ መዲናዎች፣ በጎ ተግባር ከመልካም ምኞት ባለፈ የከተማዋን ሁለንተናዊ ገፅታ የሚቀይር፣ የዜጎችን እርስ በእርስ የመደጋገፍ አቅም የሚያሳድግና የመንግሥትን የልማት ሸክም የሚያቃልል ታላቅ አቅም ሆኖ ብቅ ብሏል።
ይህ እውነትና ማኅበራዊ ካፒታል በተጨባጭ የሕዝብ ንቅናቄ ተተርጉሞ በጉልህ ከታየባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የክረምትና የበጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ውስጥ በብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የከተማዋን ነዋሪዎች ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥትን የልማት በጀት ማዳን ማስቻሉን የአዲስ አበባ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዕድሜ፣ ጾታ እና የገቢ መጠን ሳይገድበው መላው የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ ወጣቶች፣ ባለሀብቶችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከበጋ እስከ ክረምት ዓመቱን ሙሉ የሚያደርጉት ተሳትፎ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የከተማዋ ዋነኛ የኑሮ ዘይቤ አድርጎታል።
የከተማ አስተዳደሩ ይህንን አኩሪ ማኅበራዊ እሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሻገርና ዘላቂ ለማድረግም የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በማቋቋም እና ሕግ በማውጣት ተቋማዊ ቅርፅ እንዲይዝ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በመዲናዋ የሚካሄደው መጠነ-ሰፊ የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ በርካታ አቅመ-ደካሞችን፣ የሀገር ባለውለታዎችንና ለከፋ ማኅበራዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ ማስቻሉን መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፈቃደኛ የከተማዋ ነዋሪዎች በአረንጓዴ አሻራ፣ በደም ልገሳ፣ በአካባቢ ፅዳት፣ በአቅመ-ደካማ ቤቶች ግንባታና ዕድሳት፣ በትራፊክ ሕግ ማስከበር፣ በሰላም ሰራዊት፣ በምገባ ማዕከላት እና በትላልቅ የመዲናዋ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ይህ በዜጎች መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ንቅናቄም የሰዎችን እንባ ለማበስና የዘመሙ ጐጆዎችን ለማቅናት ትልቅ አቅም መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በበኩሉ፣ በ2018 በጀት ዓመት ከመስከረም እስከ ግንቦት ባሉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማስተባበር በርካታ አበይት ስኬቶችን ማስመዝገቡን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ያሉ አሮጌና ለኑሮ የማይመቹ የአቅመ-ደካማ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በአዲስ መልክ የመገንባትና የማደስ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ከዚህ በተጨማሪም የኑሮ ውድነቱን ተፅዕኖ ለመቀነስ በታላላቅ አገራዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ወቅት መጠነ-ሰፊ የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብሮች የተከናወኑ ሲሆን፣ በየወረዳው ባሉ የምግባ ማዕከላት አማካኝነትም ለሺዎች የሚሆን የዕለት ተዕለት የምሳ አቅርቦት ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የትምህርት ዘርፉን ለመደገፍና ወላጆቻቸው አቅም የሌላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ታዳጊዎች ደብተር፣ ቦርሳ፣ ዩኒፎርምና መጻሕፍት ተደራሽ ተደርጓል።

በሌላ በኩል፣ የመዲናዋን ገፅታ የቀየረውን ታላቁን የኮሪደር ልማት በበጎ ፈቃድ የማገዝ፣ አዳዲስ የሕዝብ መናፈሻዎችንና የብስክሌት መስመሮችን የመንከባከብ እንዲሁም የጤና ተቋማትን አቅም ለመደገፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ዩኒት ደም የመለገስ እና ለአረጋውያን የቤት ለቤት የሕክምና ዕርዳታ የማድረግ ሥራዎች በተሳካ ሁኔታ ተከናውነዋል።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለው መጠነ-ሰፊ የክረምትና የበጋ የበጎ ፈቃድ ንቅናቄ፣ ምሁራኑ ያስቀመጡትን በጎ ተግባር የሰውን ልጅ ጭንቀት የሚቀንስና ሰጪውንም ተቀባዩንም እኩል የሚጠቅም የሰብአዊነት መሠረት ነው የሚለውን እውነት በተግባር ያረጋገጠ ሆኗል።
በንቅናቄ የተጀመረው አኩሪ ማኅበራዊ እሴት አሁን ላይ ሕጋዊና ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ መቀጠሉ፣ መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተስማሚ የማድረጉን ጉዞ ያፋጥነዋል።
በመሆኑም፣ ይህን የጋራ የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር የመንግሥትን የልማት ሸክም የሚያቃልል ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣዩ ትውልድም የሰላምና የአንድነት ታላቅ አሻራ ሆኖ የሚቀጥል በመሆኑ መላው የከተማዋ ነዋሪ ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በአስማረ መኮንን