AMN – ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሀገርን ሠላምና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭትን እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮችን በዘላቂነት ለመግታት የሚያስችል ከ11 አጋር ተቋማት ጋር ተፈራረመ።
ባለሥልጣኑ በአዋጅ የተሰጡትን የይዘት ቁጥጥር፣ የፈቃድ አሰጣጥና የክትትል ኃላፊነቶች በተናጠል ብቻ ከመወጣት ይልቅ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ የመግባቢያ ሰነድ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በተለይም ግጭት ቀስቃሽና ከእውነት የራቁ መረጃዎች ሀገር ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከል የተቋማት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።
የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ሥነ-ሥርዓት የጦር ኃይሎች መምሪያን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን፣ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን እና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮን ጨምሮ የ11 ቁልፍ ተቋማት የበላይ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት በኩል ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ይለቀቁ የነበሩ ዘገባዎችን በማስቀር፣ የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ለመከላከል እና ሕጋዊና ኃላፊነት የሚሰማው የሚዲያ ምህዳር ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
በትባረክ ኢሳያስ