AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የሚከበሩ ሕዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት በርካታ ቱሪስቶችን እየሳቡ የሀገር ሁነኛ የሃብት ምንጭ መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የቱሪዝም ሚኒስትሯን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በጎንደር ከተማ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።
በወቅቱ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ እንደገለጹት ፤ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የሕዝብ በዓላት በርካታ የውጭ ጎብኚዎችን እየሳቡ ይገኛሉ።
የበዓላት አከባበር እሴቱና ውበቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንዲሁም ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከክልሎች ጋር በመነጋገር ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት እንዲሁም የዲጂታላይዜሽን አሠራርን የመተግበር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉን አሠራር በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የመረጃ መሠረታዊ ግብዓት በመሆኑ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በተደራጀ መልኩ የማሰባሰብ ሥራ ከክልሎች ጋር እየተከናወነ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ800 በላይ አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን መለየት የተቻለ ሲሆን ከክልል የቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በመስመር በማስገባትና በማጠናከር የዘርፉን ዕድገት የሚያፋጥኑ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ መስቀልን የመሰሉ ታላላቅ በዓላትንና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን የማካሄድ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።