የመስቀል በዓል በዓለም ላይ የሃገርን ገጽታ እና ባህላዊ ሃብታችንን ከፍ ያደረገ የጋራ እሴታችን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የመስቀል በዓል በዓለም ላይ የሃገርን ገጽታ እና ባህላዊ ሃብታችንን ከፍ ያደረገ የጋራ እሴታችን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- መስከረም 16/2019 ዓ.ም

የመስቀል በዓል በዓለም ላይ የሃገርን ገጽታ እና ባህላዊ ሃብታችንን ከፍ ያደረገ የጋራ እሴታችን ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

የ2019 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለከተማዋ ነዋሪዎች እና ለእምነቱ ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓል በከተማዋ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በሁሉም ባለድርሻዎች ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ቢኖረንም እንደ ደመራው በጋራ ስንቆም፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ስንራመድና ህብረታችንን ስናጠናክር ለከተማችንና ለሀገራችን የማይበገር ታላቅ ብርሃንና ጥንካሬ እንሆናለን ብለዋል፡፡

የመስቀል በዓል ሐይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ ሲከበር በርካታ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ሁለንተናዊ ፋይዳዎችን አቅፎ ነውም ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የመስቀል በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ በይፋ ተመዝግቦ የሰው ልጅ የጋራ የማይዳሰስ ማህበራዊ ቅርስ በመሆን በዓለም ላይ ገጽታችንን እና ባህላዊ ሃብታችንን ከፍ ያደረገ የጋራ እሴታችን ነው ብለዋል፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review