AMN- ነሐሴ 8/2018 ዓ.ም

አንድ ከተማ የምትመዘነው ለነገ ትውልድ በምትተወው ዘላቂ ልማት፥ በምትጠብቀው ተፈጥሮ፣ እና ዛሬ በምትተክለው ችግኝም ጭምር ነው።
አዲስ አበባም በዚህ የለውጥ ጉዞ ውስጥ በየዓመቱ ነዋሪዎቿን በነቂስ በማሳተፍ፣ የከተማዋን መሬት በአረንጓዴ ለመሸፈን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጥላ፣ የውበት እና የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል የከተማዋን መልክ በቀስታ ግን እጅግ ውብ በሆነ መልኩ መቀየር ጀምራለች።
ይህ ጉዞ የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን ከ2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ለማሳደግ አስችሏል።

በዚህ ውስጥ ትናንት የቆሻሻ መጣያ ስፍራዎች ዛሬ በአረንጓዴ ሲተካ፣ ትናንት በፀሐይ የሚያቃጥሉ ቦታዎች ዛሬ ጥላ ሲኖራቸው፣ ትናንት የማይታሰብ የከተማ ውበት ዛሬ የነዋሪዎቿ ዕለታዊ ሕይወት አካል እየሆነ ሲመጣ የሚታየው ለውጥ በቁጥር ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን ነው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አዲስ አበባ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የከተማ አረንጓዴነትን ከውበት በላይ ወደ የአየር ጥራት፣ የአካባቢ ጤና፣ የሕዝብ መዝናኛ፣ የከተማ ሙቀት ቅነሳ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የነገ ትውልድ የኑሮ ጥራት ጉዳይ እያሸጋገረችው ነው።
እናም የዛሬው አዲስ አበባ ችግኝ ለመትከል ብቻ የምትወጣ ከተማ አይደለችም፤ የነገውን አዲስ አበባ በዛሬ እጆቿ ለመገንባት የምትተጋ ከተማ ናት።

ከቀናት በፊትም በአንድ ጀምበር 1.5 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ለአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኛ መሆኗን እንዳሳየች የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል።
ሰው ከተፈጥሮ እየታረቀ ከአየር ጋር፣ ከውሃ ጋር፣ ከአፈር ጋር እና ከተፈጥሮ ጋር በሰላም የሚኖርባትን ከተማም በመፍጠር ላይ ናት። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መዲና ብቻ አይደለችም፤ አፍሪካን ከዓለም ጋር የምታገናኝ ከተማ ናት።
ስለዚህ የከተማዋ ውበት፣ ንፅህና፣ አረንጓዴነት፣ የመኖሪያ ምቾት እና የከተማ አቀራረብ የአዲስ አበባ ነዋሪ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይም ይሆናል።

ስለዚህ አዲስ አበባን አረንጓዴ፣ ንፁህ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እና ለመኖር ምቹ ከተማ ማድረግ የከተማ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የአገር ገጽታ ግንባታም ነው።
ዛሬ የምንተክለው ዛፍ ነገ እኛ በጥላው ስር ለመቀመጥ ብቻ አይደለም፤ ልጆቻችን እና የልጆቻችን ልጆች በንፁህ አየር እንዲተነፍሱ፣ በአረንጓዴ ከተማ እንዲኖሩ፣ በውብ አካባቢ እንዲያድጉ የምናስቀምጠው የተስፋ ፊርማ ነው።

ችግኝ ስንተክል ዛፍ ብቻ አንተክልም፤ ጥላ እንተክላለን፣ ንፁህ አየር እንተክላለን፣ ውበት እንተክላለን፣ ምግብ እንተክላለን፣ ተስፋን እንተክላለን፣ ለነገ ትውልድም ሕይወት እንተክላለን።
አዲስ አበባ የምትተክለው ችግኝ ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የተለወጠ አስተሳሰብም ጭምር ነው ። ዛሬ የምትንከባከበው ዛፍ ነገ የሚያርፍበት ትውልድ ነው።