AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም እና የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማቃለል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የህብረ-ቃል ቦሌ ሸማቾች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ተሰማ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፤ ማህበሩ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ተመራጭ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ተቋማቸው በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ በርካታ የሸማቾች ማህበራት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸው ዘይት፣ የጽዳት ዕቃዎች፣ ጤፍ፣ ዱቄት እና ስኳርን ጨምሮ የተለያዩ የቤት ውስጥ ፍጆታዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች ከጅምላ አከፋፋዮች በመረከብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ እያቀረበ መሆኑንም ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። ይሄም ገበያውን እያረጋጋ ነው ብለዋል፡፡

ከባንኮች ጋር በተደረገ ስምምነትም ግብይትን የሚያቀላጥፉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ህብረት ሥራ ጽ/ቤት ኃላፊ ትዕግስት ለታሳ በበኩላቸው፤ ማህበሩ 2 ሺህ 500 አባላትን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ ለ16 ቋሚ ሰራተኞችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

ማዕከሉ በአካባቢው ለሚኖሩ 40 ሺህ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በማህበሩ የገበያ ማዕከል ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ዱጋ ጀቤሳ፤ በውጪ ገበያ ከ200 እስከ 220 ብር የሚሸጠው ስኳር በማህበሩ በ169 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጥራጥሬ፣ በቡና እና በፓስታ ምርቶች ላይ ከ10 እስከ 25 ብር የሚደርስ የዋጋ ቅናሽ መኖሩ ለሸማቾች ትልቅ እፎይታ መስጠቱንም ገልጸዋል፡፡
ሌላኛዋ ሸማች ወይዘሮ ጸሐይ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ረገድ ከውጪው ገበያ ከፍተኛ ልዩነት እያሳየ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ደረጃ ብቻ ከ257 በላይ የሸማቾች ማህበራት የሚገኙ ሲሆን ከ800 በላይ መደበኛ ሰራተኞችን ጨምሮ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ከ1 ሺህ 779 በላይ ለሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ተመላክቷል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ